የካቲት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ለአራት ቀናት ውይይት በአዲስ አበባ አካሂደዋል።

በውይይታቸውም በክልሉ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍቻ መንገዶች፣ አቅጣጫ፣ መፍትሔና አቋም አስቀምጠዋል።

አሐዱ ያነጋገራቸው የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲ (ኢፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ ገመቹ "በክልሉ የሚስተዋለውን ግጭት እንዴት እንፍታው? ሰላምን እንዴት እናምጣ? በሚል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጨምሮ አባገዳዎች፣ ዋቄ ፈናዎች እና የሃይማኖት አባቶችን በተገኙበት ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

በዚህም በኦሮሚያ ክልል ያለው ግጭት እንዲቆም በክልሉ ያለው ታጣቂ ሃይል ከመንግሥት ጋር ቁጭ ብሎ የሚወያይበት መንገድ መፈጠሩን አንስተዋል።

ኦፌኮ እና ኦነግ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን "የኦሮሚያ የሽግግር መንግሥት ለመመስረት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደ ኦሮሞ ነፃነት ታጋዮች በሽግግር መንግሥት ስልጣን ሥር የኦሮሚያን ሰላም፣ ፀጥታ እና ወሰን የማስጠበቅ ሃላፊነት እንደሚሰጠው ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉ ሁሉም ብሄረሰቦች ያለምንም አድልዎ እንዲኖሩ ለማስቻል እንደሚሰሩም አንስተዋል።

በዚህም በክልሉ የሚስተዋሉ ግጭቶችን ለመፍታት እና ሰላም ለማስፈን ሁለቱ አካላት ማንኛውንም መንገድ በመጠቀም ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቃል ገብተዋል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) በሽግግር መንግስቱ ኃላፊነት ወስዶ ሰላምና ደህንነት እንዲሁም የኦሮሚያን ወሰን የማስከበር ኃላፊነት እንዲወጣ ሁለቱ ፓርቲዎች አስፈላጊውን ዝግጅት እንደሚያደርጉም ተመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ