የካቲት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አቅም ያላቸው ግለሰቦች በአሜሪካ ቋሚ የመኖሪያ ፍቃድ እንዲያገኙ የሚያስችል "ወርቃማ ካርድ" በ5 ሚሊዮን ዶላር ለሽያጭ አቅርበዋል።

ይህ አዲስ የትራምፕ እቅድ በአሜሪካ መዋዕለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ ግለሰቦች ይሰጥ የነበረውን ነባር የመኖሪያ ፍቃድ (ግሪን ካርድ) ፕሮግራም ያስቀራል ተብሏል።

ፕሬዝዳንቱ በትናትናው ዕለት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ የቪዛ ፕሮግራምን ለውጭ ባለሃብቶች በ5 ሚሊዮን ዶላር ለመሸጥ በሚያስችል "የወርቅ ካርድ" የመተካት ሀሳባቸውን አንስተዋል።

ትራምፕ በመግለጫቸው፤ በሀገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ የሚያመጡ ወይንም በአሜሪካ የሥራ ዕድልን የሚፈጥሩ የውጭ ባለሃብቶች ቋሚ ነዋሪ እንዲሆኑ የሚያስችለውን "ኢቢ-5" የስደተኛ ኢንቨስተር ቪዛ ፕሮግራም፤ በ"የወርቅ ካርድ" እንደሚተኩ ተናግረዋል።

የኢቢ-5 ፕሮግራም በአሜሪካ ንግዶች ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ለሚገቡ የውጭ ዜጎች "አረንጓዴ ካርዶች" ይሰጣል።

"የወርቅ ካርድ ልንሸጥ ነው" ያሉት ትራምፕ፤ "በዚያ ካርድ ላይ ወደ 5 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ እንጥላለን" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ይህም በአረንጓዴ ካርድ ይሰጡ የነበሩትን ልዩ መብቶችን እና የአሜሪካ የዜግነት ዕድሎችን እንደሚያስገኝ የገለጹ ሲሆን፤ "ሀብታም ሰዎች ይህንን ካርድ በመግዛት ወደ አገራችን ይመጣሉ" ብለዋል።

'እነዚህ ባለሃብቶች ክፍያውን ለመፈጸም ብቁ ይሆናሉ ወይ?' ተብለው በጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ትራምፕ ሲመልሱ፤ እ.ኤ.አ. በ 1991 በሶቪየት ኅብረት ውድቀት ወቅት ብዙ ሀብት ያፈሩት (የሩስያ ኦሊጋርቾች) ለወርቅ ካርዶቹ ግዢ ብቁ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ይህም 5 ሚሊየን ዶላር የመክፈል አቅም ላላቸው የሚቀርበው ወርቃማው ካርድ በቀጣዮቹ 3 ሣምንታት ውስጥ ለገዥዎች ክፍት እንደሚሆን ተነግሯል።

በአሜሪካ የዜግነት እና ኢሚግሬሽን አገልግሎት የሚተዳደረው ኢቢ-5 የስደተኛ ባለሀብት ፕሮግራም፤ "የአሜሪካን ኢኮኖሚ በሥራ እድል ፈጠራ እና በውጭ ባለሃብቶች የካፒታል ኢንቨስትመንት ለማበረታታት" በሚል በአውሮፓውያኑ 1990 በኮንግረስ ጸድቆ ተግባራዊ የተደረገ አሰራር ነው፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ