የካቲት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የሙትአንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል ገዳም ከሀገር ውስጥ እና በውጭ ካሉ ሕዝበ ክርስቲያናት 11 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ እና የአይነት ድጋፍ ማግኘቱ ተገልጿል።
በተጨማሪም ገዳሙ አንድ ሚሊዮን 200 ሺሕ ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ እንዳገኝ አስታውቋል።
እንዲሁም ለገዳሙ አስፈላጊ እና መሰረታዊ የሆኑትን የልማት ሥራዎችን ለማከናወን የሚያስችል ገቢ ለማሰባሰብ፤ ከመጋቢት 25 እስከ ሚያዝያ ሁለት ቀን 2017 ዓ.ም ወደ ገዳሙ የበረከት ጉዞ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
የገዳሙ አባቶች በተሰበሰበው ገንዘብ በገዳሙ ውስጥ ለሚገኙ እናቶች መጠለያ ቤት እንደተሰራ ገልጸው፤ እንዲሁም 170 ሜትር ተራራ ተቦርቡሮ በገዳሙ ለሚገኝ ለመለኮሳቱ እናቶች እና ለአባቶች ምቹ የሆነ መንገድ እንደተሰራ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ገዳማዊያኑ በተደጋጋሚ የሚገጥማቸውን የምግብ አቅርቦት ችግር እና የአቅም ውስንነት በዘላቂነት ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።
ለገዳማዊያኑ የእደ - ጥበብ ውጤቶችን ማምረቻ ሼድ ግንባታ ተከናውኗል እንዲሁም፤ የሸማ ሥራ ሙያ እንዲሰለጥኑ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል ሲሉ አስታውቀዋል። የሻማ እና የጧፍ መስሪያ ማሽን ግዢ እንደተከናወነ ለአሐዱ ተናግረዋል።
አካባቢው በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቃ በመሆኑ ለገዳማዊያኑ የተሻለ ለማድረግ የአካባቢው ጥበቃ ሥራዎች እየተሰራ እደሚገኝ ገልጸዋል።
ወደ ገዳሙ የሚወስድ 8 ኪሎ ሜትር ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ሥራ ተሰርቶል ሲሉም ገልጸዋል።
እንዲሁም የእናቶች መፀዳጃ ቤት እንደተገነባ አስታውቀው፤ እነዚህ ሁሉ ሥራዎች ቢሰሩም አሁንም በገዳሙ ያለው ችግር እንዳልተቀረፈ እና በርካታ ሥራዎች እደሚቀሩ የገዳሙ አባቶች አስረድተዋል።
የሙት አንሳ ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም እነዚህን ሥራዎች ሲሰራ በርካታ ችግሮች ገጥሞት እደነበርም የገዳሙ አባቶች ጨምረው ለአሐዱ ተናግረዋል።
ገዳሙ ከገጠመው ችግር መካከል የአካባቢው የሰላም እጦት ውስጥ መሆኑ፣ የግንባታ እቃዎች መጨመር እንዲሁ የማህበራዊ ሚዲያ የሚጠቀሙ አንዳንድ አካላት የገዳሙን ሥም የማጥፍት ዘመቻ ማድረጋቸው እንደሚገኙበት ገልጸዋል።
የገዳሙን ሥም ያጠፉ የማህበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች ገዳሙ ከሶ በራሳቸው ወጭ ገዳሙ የደረሰበትን ደረጃ እንዲያዩ ተደርጓል ሲሉም የገዳሙ አባቶች ለአሐዱ ተናግረዋል።
በቀጣይም ጥቅምት 16 ቀን 2018 ዓ.ም በሚሊኒየም አዳራሽ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን በተገኙበት ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃግብር እንደሚዘጋጅ ተነግሯል።
በማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት በሚገኘው የሙት አንሳ ማር ቅዱስ ሚካኤል አንድነት ገዳም ከ90 በላይ መነኮሳት የሚገኙ ሲሆን፤ ገዳሙ ካለበት አካባቢ አንፃር ለከፍተኛ ችግር በመጋለጡ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በገዳማውያኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በህይወት ጌትነት
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በገዳሙ 11 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡ ተገለጸ
