የካቲት 19/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በግንባታ ወቅት የሚደርሱ አደጋዎችን ለመከላከል እና የሕንጻ ደረጃን ለማስጠበቅ ከአልሚዎች በተጨማሪ የዘርፉ አማካሪዎችንና የስነ ሕንጻ -ንድፍ ባለሙያዎች ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድ ቁጥጥር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛህኝ ደሲሳ፤ ረዘም ያለን ጊዜን በሥራ ላይ በመቆየት እና አብሮ በመስራት በሚፈጠር ትውውቅ፤ በግንባታ የሥራ ሂደት ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር በዘርፉ ባለሙያዎች፣ በአልሚዎች እና በስነ ሕንጻ -ንድፍ ሙያተኞች ላይ ድንገተኛ የሆነ ቁጥጥር እየተካሄደ እንደሚገኝ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የአንድን ሕንጻ ከፍታው እንዲሁም ሕንጻው መገንባት ያለበት ቦታን በተመለከተ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከአልሚዎች ጋር ስምምነት እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡
አክለውም "ከስምምነት በኋላ ወደ ግንባታ በሚገባበት ወቅት ለአሊሚዎች ወይም ለዘርፉ ባለሙያዎች ፈቃድ በወሰዱበት የግንባታ መሠረት እንዲሁም ዲዛይን መሠረት የሕንጻ ግንባታ እንዲያከናውኑ በባስልጣን መስሪያ ቤቱ ቁጥጥር ይደረጋል" ብለዋል፡፡
በመሆኑም በተፈቀደው መሠረት ግንባታው እየተከናወነ ስለመሆኑ በዘርፉ ባለሙያ እና በአልሚዎች ላይ ድንገተኛ የሆነ የክትትል ሂደት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአገልግሎት ላይ የነበረው የሕንጻ አዋጅ በባለስልጣኑ በሚከናወነው የቁጥጥር ሂደት ላይ እንደ ክፍተት የሚነሳ እንደነበር የገለጹም ሲሆን፤ ከአልሚዎች ውጪ ሌሎች በግንባታ ሂደቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ተጠያቂ የማይኑበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተሻሻለው የአሰራር ሂደት ላይ በግንባታ ወቅት በሚከሰቱ አደጋዎች አልሚዎች ብቻ ሳይሆኑ የዘርፉ ባለሞያዎች እና ኮንትራክተሮች ተጠያቂ እየሆኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ሰዓት ረዘም ያለ ጊዜን በሥራ ላይ በማሳለፍ በአልሚዎች፣ በስነ ሕንጻ -ንድፍ ሙያተኞች እንዲሁም የዘርፉ ባለሙያዎች ላይ በሚፈጠር ትውውቅ ምክንያት፤ በሥራ ሂደቱ ላይ ክፍተቶች እንዳይፈጠር ድንገተኛ የሆነ ምልከታ በግንባታ ቦታ ላይ እየተከናወነ ይገኛል፡፡
አክለውም በክትትል የሥራ ሂደት ላይ ከፍቃድ ውጪ ግንባታዎች ተከናውነው ከተስተዋሉ በአልሚዎች ላይ የገንዘብ ቅጣት እንዲሁም በስነ ሕንጻ -ንድፍ ሙያተኞች እና በዘርፉ ባለሙያዎች ላይ ፍቃድ እስከ መሰረዝ የሚደርስ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
አቶ ገዛሕኝ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙ አልሚዎች ላይ እስከ 6 ሚሊየን ብር የሚደርስ ቅጣት የሚጣልበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት በ2016 ዓ.ም ወደ ትግበራ በተገባው የሕንጻ አዋጅ ማሻሻያ እስከ 65 ሚሊየን ብር ቅጣት ስለመጣሉ አስታውቀዋል፡፡
በወር ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በግንባታ ወቅት ላይ በሚደርሱ አደጋዎች ምክንያት ቅሬታ ያቀርቡ እንደነበር የገለጹም ሲሆን፤ በሚወሰዱ እርምጃዎች የቅሬታ አቅራቢዎችን አሃዛዊ ቁጥር መቀነስ ስለመቻሉም ተናግረዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በግንባታ ወቅት ለሚደርሱ አደጋዎች ከአልሚዎች በተጨማሪ የዘርፉ አማካሪዎች እና የስነ ሕንጻ -ንድፍ ባለሙያዎች ተጠያቂ እየተደረጉ መሆኑ ተገለጸ
