መጋቢት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ባለፉት ወራት በሕዝብ ማመላለሻ ውስጥ እየተፈጸመ ያለው የስርቆት እና የዝርፊያ በተለምዶ (ሿሿ) እየተባሉ የሚጠሩት ወንጀሎች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮማንደር ማርቆስ ታደሰ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ለወንጀሉ መቀነስ ምክንያት የሆነው የፖሊስ ርምጃዎች ተጠናክረው በመቀጠላቸው፣ ከፍተኛ ቁጥጥርና ክትትል በመደረጉ እንዲሁም የሕብረተሰቡ ግንዛቤ በመጨመሩ ነው።
ኮማንደር ማርቆስ አክለውም ወንጀለኞች እነዚህን ወንጀሎች ለመፈጸም የተለያዩ የማታለያ ዘዴዎችን የሚጠቀሙ ሲሆን፤ ራሳቸውን እንደ ተራ ተሳፋሪ፣ የተማሩ እና የሃይማኖት አባቶችን በመምሰል ድርጊቱን ይፈጽማሉ። "በተጨማሪም ሴቶችም በእነዚህ የወንጀል መረቦች ውስጥ ተሳታፊ ናቸው" ብለዋል።
በየጊዜው የስርቆት ወንጀል መልካቸውን እየቀየሩ መምጣታቸውን በማንሳትም፤ በወንጀሉ የሚሳተፉ ሴቶች ቁጥርም በዛው ልክ እየጨመሩ መምጣታቸውን አንስተዋል።
"ከግል የማስመሰል ስልቶች በተጨማሪ ወንጀለኞቹ የተሽከርካሪዎችን ታርጋ ይቀይሩ ነበር" ያሉት ኮማንደር ማርቆስ፤ ታርጋ በማጠፍ እንዲሁም ቀለም በቀባትና ለሌሎች እንዳይነበቡት በማድረግ ለመለየት እና ለመያዝ አስቸጋሪ ሆነው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ፖሊስ እነዚህን እንቅስቃሴዎች ለመከላከል ተከታታይ ጠንካራ ጣልቃ ገብነቶችን መጀመራቸውን በመግለጽ፤ እንዲህ አይነት ወንጀሎች በብዛት የሚፈጸሙባቸውን ቦታዎች በመለየትና ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ወንጀሉን የመቀነስ ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
"በተጨማሪም የተደበቀ ወይም የተቀየሩ ታርጋ ያላቸው ተሽከርካሪዎችን በቅርበት እየተከታተልን ነው።" ያሉት ኮማንደር ማርቆስ፤ ፖሊስ እነዚህን ሥራዎች ከሕብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ዘመቻዎች ጋር በማጣመር የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ዜጎች እራሳቸውን እንዴት እንደሚከላከሉ እና አጠራጣሪ ድርጊቶችን ማሳወቅ እንደሚችሉ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
"በወንጀለኞች ላይ ጥብቅ ህጋዊ እርምጃም ሆነ የማስተካከያ እርምጃ እየተወሰደ ነው" ሲሉ ኮማንደር ማርቆስ ጨምረው ገልጸዋል።
"የእኛ ጥምር ጥረታችን በማህበረሰብ ተሳትፎ፣ ክትትል እና ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት፤ ከሕዝብ ትራንስፖርት ጋር የተያያዘ ስርቆትን በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ውጤቶችን እያሳየ ነው" ብለዋል፡፡
ይህንን መልካም አዝማሚያ ለማስቀጠል ሕብረተሰቡ ነቅቶ እንዲጠብቅና ከሕግ አስከባሪ አካላት ጋር ያለውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ አሳስቧል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ