መጋቢት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቀላል ባቡሮች ላይ የሚያጋጥሙ ብልሽቶችን ጠግኖ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል፤ የግብዓት አቅርቦት እጥረት ከፍተኛ ተግዳሮት እየሆነበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል፡፡

የቀላል ባቡሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርሃን አበባው (ዶ/ር) ለአሐዱ እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በከተማዋ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የቀላል ባቡር ትራንስፖርቶች 19 ሲሆኑ፤ በቀን በአማካይ ከ50 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የትራንስፖርት አገልግሎት ይሰጣሉ።

Post image

"ይህም አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮች ቁጥር ካለው የትራንስፖርቱ ተጠቃሚ አንጻር በቂ ነው ማለት አይቻልም" ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ከሥራ ውጪ የሆኑ ባቡሮችን ወደ ሥራ ለመመለስ የመለዋወጫ አቅርቦት እጥረቱን መፍታት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።

በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግሮች ስለመኖራቸው እና ይህም በሥራ ሂደቱ ላይ ተግዳሮት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የትራንስፖርቱ የትኬት መሸጫ ጣቢዎች ከባቡር ፌርማታዎች አንዳንዶቹ በርቀት ላይ የሚገኙ ስለመኖራቸው የተናገሩም ሲሆን፤ ይህን ችግር ለመፍታት ከዛሬ ሰኞ መጋቢት 8 ቀን 2017 ጀምሮ የዲጂታል የትኬት ሽያጭ እንዲከናወን ለማድረግ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡

የዲጂታል ትኬት የክፍያ ስርዓቱ በቴሌ ሱፐር አፕ እና በዩኤስ ኤስዲ (USSD) ኮድ አማካኝነት መቁረጥ እንደሚያስችል በመግለጽ፤ ደንበኞች የትኛውንም አይነት ስልክ በመጠቀም አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ ተደርጎ መጀጋጀቱንም ጠቁመዋል።

አክለውም ከዚህ ቀደም የነበሩት የባቡር ትኬት መሸጫ ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የሚጀመረው የዲጂታል የትኬት ሽያጭ በዳግማዊ ምኒልክ፣ ስታዲየም፣ ቃሊቲ ፣ጦር ኃይሎች እና ሀያት መስመሮች በአጠቃላይ በ5 የትኬት መሸጫ ጣቢያዎች ይከናወናል ብለዋል፡፡

አክለውም ለአገልግሎቱ የሥራ ሂደት ወደ 30 የሚጠጉ ባለሙያዎች እንደተዘጋጁ ገልጸዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው በተያዘው ዓመት 6 የከተማ ቀላል ባቡሮችን ጠግኖ አገልግሎት ላይ ማዋል ስለመቻሉም የገለጹ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ያለው ቀላል ባቡር 13 እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አክለውም በቀጣይ 21 ቀላል ባቡሮች አግልገሎት እንዲሰጡ ለማድረግ በእቅድ ስለመያዙ ተናግረዋል።

የቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት በአዲስ አበባ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ለመቅረፍ ታቅዶና ከ475 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ወጭ ተደርጎበት፤ በ2008 ዓ.ም ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል።

ሆኖም የቀላል ባቡር አገልግሎቱ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ፤ በየጊዜው በትራንስፖርት መስተጓጎል ችግር ምክንያት በኅብረተሰቡ ዘንድ የተለያዩ ቅሬታዎች ሲነሱበት ይደመጣል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ