መጋቢት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአዲስ አበባ ግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን ባወጣውና ከ2015 ጀምሮ ሥራ በሚገኘው መመሪያ መሠረት፤ በሕንጻ ግንባታ ወቅት የአደጋ ጊዜ መውጫን ጨምሮ አሳንሰር እና ሌሎች የግንባታ መስፈርቶችን በማያሟሉ ገንቢዎች ላይ ከሚጣለው ቅጣት የሚሰበሰበው ከ3 እስከ 5 ሚሊየን ብር ገቢ ወደ 65 ሚሊየን ብር ከፍ ማለቱ ተገልጿል፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ ደሲሳ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ ይህ ከቅጣት የሚገኘው ገቢ ከፍ ሊል የቻለው፤ መመሪያዎችን የማያሟሉ አካላትን ቁጥር ለመቀነስ እንዲሁም ሕንጻዎች በዲዛይንም ሆነ በግንባታ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ ለማድረግ እየተወሰደ ባለው ጥብቅ ቁጥጥር ምክንያ ነው።

"በከተማዋ በ2016 በተደረገ ዳሰሳ ከ52 ሺሕ 600 በላይ ሕንጻዎች ይገኛሉ" ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ በእነዚህ ሕንጻዎች ላይ በየአራት ዓመቱ የሚደረገው ፍተሻ አሁን ወደ ሁለት ዓመት ዝቅ እንዲል መደረጉን ጨምረው ተናግረዋል፡፡

አሐዱም "በዚህ አሠራር መሠረት ምን ያክል ገንቢዎች ተጠያቂ ተደረጉ?" ሲል ላነሳው አቶ ገዛኸኝ ሲመልሱ፤ በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 36 የሕንጻ መለያ እና ደረጃ ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦች ቅጣት እንደተጣለባቸው ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ቅጣት የተላለፈባቸው ግለሰቦች ኮንትራክተሮች፣ የሕንጻ ግንባት አማካሪዎች፣ የወረዳ አመራሮች እንዲሁም ባለሙያዎች መሆናቸውን የገለጹም ሲሆን፤ ከቅጣቱም ከ61 ሚሊየን 321 ሺሕ ብር በላይ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

አክለውም፤ "ከሕንጻዎች የአደጋ ጊዜ መውጫ ብረቶች መስፈርት (ስታንዳርድ) ጋር በተያያዘ የሚወስነው ቅጣትም የሕንጻው ከፍታና የሚይዘው ክብደት ላይ ተመስርቶ ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ይህ መስፈርት የሚሰራው ለአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከ12 ሜትር እና ለመኖሪያ ቤቶች ከ20 ሜትር በላይ የሆኑ ሕንጻዎች ላይ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ