መጋቢት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በ2017 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት ከ168 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከሕገ ወጥ የጎዳና ላይ ነጋዴዎች መሰብሰቡን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የባለስልጣኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የምስራች ግርማ ለአሐዱ እንደገለጹት፤ በደንብ ማስከበር ሂደቱ በሕገ-ወጥ የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተው በሚገኙ ግለሰቦች ላይ የሚጣልባቸው ቅጣት ከዓመት ወደ ዓመት በእጥፍ እንዲጨምር ተደርጓል፡፡

አሐዱም በደንብ ማስከበር ዘመቻ ወቅት፤ በአንድም በሌላም መልኩ የሚወረሱ ንብረቶች ለምን አገልግሎት እየዋሉ ነው? ምን ያህልስ መሰብሰብ ተችሏል? ሲል የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተሯን ጠይቋል፡፡

በምላሻቸውም በግማሽ ዓመቱ ብቻ ከ160 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን በመግለጽ፤ "የሚወረሱ ምርቶችም ለልማት እንዲውሉ እየተደረገ ነው" ብለዋል፡፡

"በተጨማሪ በየወረዳው የሚወረሱ ንብረቶችን እያንዳንዱ የወረዳው ኮሜቴ በጥንቃቄ በመመዝገብ ለባለስልጣኑ ካስረከበ በኃላ በሽያጭ ሂደቱ ላይ እንደ ኮሜቴ ሆነን እንሳተፋለን" ያሉት ዳይሬክተሯለ በቀጣይ ግን ባለስልጣኑ ራሱን ችሎ በጨረታ የሚሸጥበትን የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት እየሰራ መሆኑን ለአሐዱ ጠቁመዋል፡፡

ደንብ የማስከበር ሥራ ለአንድ ተቋም ብቻ የሚሰጥ እንዳልሆነ ያነሱም ሲሆን፤ እያንዳንዱ ማሕበረሰብ በሕገ-ወጥ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ለተቋሙ የመጠቆም እንዲሁም ድርጉቱን የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ