መጋቢት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በተያዘው የ2017 ግማሽ ዓመት የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ሳይኖራቸው እንዲሁም በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ የተገኙ 1 ሺሕ 530 አሽከርካሪዎች እርምጃ እንደተወሰደባቸው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
በኮሚሽኑ የትራፊክ ቁጥጥር መምሪያ የትራፊክ ሙያና ሕዝብ ግንዛቤ ዲቪዝን ኃላፊ ኢንስፔክተር ሰለሞን አዳነ፤ እርምጃዎቹ በአዋጅ ቁጥር 1074/2010 ዓ.ም በወጣው መመሪያ የተደነገጉ ደንቦችን ተግባራዊ ለማድረግ በተደረገው ቁጥጥር መሠረት የተወሰዱ መሆናቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል።
በተለይ 'የማሽከርከር ፍላጎት ሳላላቸው ብቻ' ንብረታቸውን ለሌላ አካላት አሳልፈው በመስጠት በመንገድ ላይ እንዲያሽከረክሩ በሚፈቅዱት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑንም አያይዘው ገልጸዋል፡፡
ኃላፊው አክለውም የአሽከርካሪ ብቃት ፈቃድ ሳይኖራቸው ሲያሽከረክሩ የተገኙ 1 ሺሕ 140 ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዱን የገለጹ ሲሆን፤ በሐሰተኛ መንጃ ፈቃድ ሲያሽከረክሩ የተገኙ 394 አሽከርካሪዎች ላይ የተወሰዱ ቅጣቶች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡
የእርምጃ አወሳሰዱን በተመለከተ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ሳይኖረው በሚያሽከረክሩ ላይ እስከ 8 ሺሕ ብር ቅጣት እንዲሁም ለሌላ አካላት አሳልፎ መስጠት ደግሞ እስከ 3 ሺሕ ብር ቅጣት የተወሰደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አክለውም የትራፊክ አደጋ መንስኤ ከሆኑት ዋነኛ ጉዳዮች መካከል ያለ መንጃ ፈቃድ ማሽከርከር ተጠቃሽ መሆኑን በመግለጽ፤ በዚህም ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
እንዲሁም የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ ሁሉም ማህበረሰብ የሚወጡ መመሪያዎችን በማክበር የጋር ትብብር በመፍጠር መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ሳይኖራቸው በሚያሽከረክሩ ከ1 ሺሕ 500 በላይ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መውሰዱ ተገለጸ
