መጋቢት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፖርቲ (ትዴፓ) በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት በፖርቲው ፅህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ፤ "ህወሓት ትግራይን ዳግም ወደ ጦርነት ሊወስዳት እየሞከረ ነው" ሲል አስታውቋል።

መግለጫውን የሰጡት የፖርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ሲሆኑ፤ በትግራይ ክልል የጦርነት ደመና እያንዣበበ በመሆኑ የተሰጠ መግለጫ መሆኑን ተናግረዋል።

"በተለይም ይህ ጦርነት እንዲመጣ የሚቀሰቅሱ አካላት በመኖራቸው እነዚህ አካላት አደብ እንዲይዙ በማሰብ የተሰጠ ነው" በማለት ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

Post image

"አንዱ የህወሓት ቡድን 'ስልጣን አጣለው' የሚል ፍርሀት ስላለው የፕሪቶሪያዉ የሰላም ስምምነት እንዳይተገበረ በቻለው መጠን እየሞከረ ነው" ሲሉም ሊቀመንበሩ ተናግረዋል።

"የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አካታች የሆነ ግዜያዉ አስተዳደር እንዲፈጠር የሚፈቅድ ቢሆንም፤ ህወሓት ግን ሁሉንም የአስተዳደር ስልጣን ወደ ራሱ በመውሰድ ፍትሀዊ የአስተዳደር ሂደት እንዳይኖር አድርጓል" ብለዋል።

በዚህም ትግራይ ዳግም ወደ ጦርነት እንድትገባ የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ፤ የፌደራል መንግሥቱም ይህ ስምምነት ላለመተግበሩ ተጠያቂ ነው ሲሉም በመግለጫው ወቅሰዋል።

ትዴፖ 'በትግራይ ላይ ጦርነት በድጋሚ መምጣት የለበትም' የሚል ፅኑ አቋም እንዳለው የገለጸ ሲሆን፤ ከዚህ በተጨማሪ "የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ ለሙሉ ሊተገበር ይገባልና አፅንኦት ይሰጠው" ብሏል።

"ይህ 'ጦርነት ፈላጊ' ተብሎ የተጠቀሰው ቡድን በግልፅ የትኛውን የህወሓት ቡድን ነው?" ሲል አሐዱ የፓርቲውን ሊቀመንበር ዶ/ር አረጋዊ በርሄን ጠይቋል።

ሊቀምንበሩ ይህንን ሲመልሱም፤ ከኤርትራ ሃይሎች ጋር ግነኙነት ያለው፣ እንደውም ትግራይ ውስጥ የኤርትራ ሀይሎች ዘልቆ እንዲገቡ የፈቀደው ቡድን ነው" ብለዋል።

"የፕሪቶሪያው ሥምምነት ሲፈረም ህወሓት አንድ የነበረ ቢሆንም አንዱ ከፌደራል መንግሥት ጋር በመተባበር ስምምነቱን እንዲተገበር ሲጥር፤ በሌላ በኩል የሚመራው ቡድን ግን ከዚህ በተቃራኒ እየሄደ ነው" ሲሉም ኮንነዉታል።

"ይህ ሲባል ግን አቶ ጌታቸዉ ረዳ የሚመራው ግዚያዊ አስተዳደር በርካታ ችግር ቢኖርበትም በአንፃራዊነት ጦርነት እንዲቆም አድርጓል" ብለዋል።

ሌላው "ትግራይ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ወዲህ አሁንም ድረስ ከፍተኛ ችግር ውስጥ መሆኗ ይታወቃል። ለመሆኑ እንዲህ ያለውን መግለጫ ለመስጠት ፖርቲው አልዘገየም ወይ?" ሲል አሐዱ ለጠየቅነው ጥያቄ ሊቀመንበሩ ሲመልሱ፤ "አልዘገየንም" ብለዋል።

"ከመጀመሪያው ጀምሮ የፕሪቶሪያዉ የሰላም ስምምነት ሙሉለሙሉ እንዲተገበር በሚል ጥሪዎችን አድርገናል" ሲሉም ለአሐዱ መልሰዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ውስጥ ገብተው እንዳይንቀሳቀሱ እና ጥረት እንዳያደርጉ በአንዱ ህወሓት ቡድን ጫና እንደነበረባቸዉ በመግለፅ፤ አሁን ቢያንስ ቢሮ መክፈት መቻሉን ገልጸዋል።

በመሆኑም የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ጉዳይ በተለይም ፕሪቶሪያው ሰላም ስምምነት እንዲተገበር ቁርጠኛ መሆን አለበት ተብሏል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ