ጥር 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የመንግሥት ሥራዎችን የሚከታተሉ 22 ትይዩ የካቢኔ ሚኒስትሮችን አዋቅሮ ሥራ ማስጀመሩ የሚታወስ ነው።

ይህ ትይዩ ካቢኔ የዕለት ከዕለት የመንግሥት ተግባራትን መከታተል፣ የሚወጡ ረቂቅ ሕጎችን መገምገም፣ የፖሊሲ ንድፈ ሐሳቦችን ማውጣትና መሰል ሥራዎችን ያከናውናል። አሐዱም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ፓርቲውን አነጋግሯል፡፡

የፓርቲው ምክትል መሪና የሕንጻ ንድፈ ሀሳብ ባለሙያ አቶ ዮሐንስ መኮንን "የትይዩ ካቢኔ መዋቀር ለዲሞክራሲ፣ ለሀገራዊ ለውጥ እንዲሁም ሀገሪቱ እንድትሄድበት በሚፈልገው የልማት ጉዞ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል" ብለዋል፡፡

ትኩረት በሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች የፖሊሲ አቅጣጫ ከመስጠት እስከ ሙያዊ ዝርዝር ጥናቶች በማቅረብ ምክር ሃሳቦችን ለመንግሥት እንደቀረበ አንስተው፤ ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር በተያያዘም ለመንግሥት እና ለሕዝብም ማሳወቁን ገልጸዋል፡፡

"የካቢኔ አባላት በሕግ አውጪ ወይም በሕግ አስፈጻሚ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ በማድረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ለሰላምና ልማትን ለማምጣት አስተዋጾ አለው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

አክለውም "በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አዲስ ልምድ በመሆን ለቀጣይ ምርጫ እራሳችንን እንድናዘጋጅ እና በቂ ልምድ አግኝተናል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የትይዩ ሚኒስትሮች ማንነትና ኃላፊነትን በተመለከተ ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል፡፡

ኃላፊው አያይዘውም የትይዩ ካቢኔ አባላት በሌሎች ዓለም ሀገራት የግድ የፓርቲ አባል መሆን እንደማይጠበቅባቸውና የባለሙያዎች፣ የሙሁራን ሰብስብ በመሆኑ ለመንግሥት ምክር ሐሳብ ማቅረብ እንደሚችሉ በማንሳት፤ በኢትዮጵያ ግን ይሄ ተቃራኒ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የካቢኔ አባላቱ ፓርቲውን ተፎካካሪ በማድረግ ዋነኛ የሥራ ድርሻቸውን እንደተወጡ ገልጿል።

'የኢዜማ አመራሮች እና አባላት ሥልጣን ማግኘታቸው ተፅዕኖ አያሳድርም' ለሚሉ ሀሳቦች ሕጋዊ መሆኑን ገልፀው፤ ይህም የመንግሥት ሥራን ለመከታተል ምቹ መደላደል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡

እንዲህ አይነቱ የተቃዋሚ ትይዩ የካቢኔ ሚኒስትሮች ካሏቸው መካከል ዩናይትድ ኪንግደም፣ አውስትራሊያ፣ ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያንና ጃፓን የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ከአፍሪካም በደቡብ አፍሪካና ሱዳን ውስጥ የተቃዋሚዎች ትይዩ ካቢኔ አላቸው ብለውናል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ