የካቲት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ "የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ዘርዓ አፍሪካውያን" በሚል መሪ ሀሳብ፤ ዛሬ በአዲስ አበባ መካሄድ ይጀመራል።
በዚህም ጉባዔው የካቲት 5 እና 6 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው 46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ወቅት በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ይመክራል ልዩ ልዩ ውሳኔዎችንም ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም የአፍሪካ ሕብረት ተቋማዊ ማሻሻያዎች፣ የማካካሻ ፍትህ፣ አፍሪካ በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ለማግኘት እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም አህጉራዊ ሰላምና ደህንነት አጀንዳዎች ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡
ጉባዔው የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና አፈጻጸምና አህጉራዊ የንግድና ኢኮኖሚ ትስስር፣ ግብርናና የአየር ንብረት ለውጥ፣ ሰብዓዊ መብቶች፣ ስርዓተ ጾታና ወጣቶችን ማብቃት እንዲሁም የተቋማት አደረጃጀቶች ላይ ጉባኤው ይወያያል ተብሎም ይጠበቃል።
በጉባኤው ለመሳተፍ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።
በዛሬው ዕለት በአዲስ አበባ የሚጀመረው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ እስከ ነገ ድረስ ይቆያል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ ይጀመራል
