የካቲት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅና አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፤ የ40ኛው ዙር የሕክምና ተማሪዎች እና 21ኛው ዙር የፋርማሲ ተማሪዎች የምርቃት መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት አካሂዷል፡፡

ዩንቨርስቲው በመጀመሪያ ዲግሪ፣ በሁለተኛ ዲግሪ በሦስተኛ ዲግሪ፣ በስፔሻሊቲ እና ሰብ ስፔሻሊቲ የትምህርት ዘርፎች፤ በአጠቃላይ 254 ወንድ እና 112 ሴት በድምሩ 366 ዕጩ ምሩቃንን ነው በዛሬው ዕለት ያስመረቀው፡፡

Post image

በምርቃት መርሃ ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጄ ድጉማ፣ የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን፣ የጎንደር ከተማ ከንቲባና የዩንቨርስቲው ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሮ ደብሬ የኋላ፣ የሕዝብ ተወካይ ምክር ቤት አባላት፣ የዩንቨርስቲው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ተመራቂ ተማሪዎች እንዲሁም የተመራቂ ተማሪ ወላጆች ተገኝተዋል፡፡

Post image

የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አስራት አጸደወይን በመርሃ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በቅድመ ምረቃ እና በድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎች በኮሌጅ የትምህርት ጉባዔ ተመስክሮና በዩንቨርስቲው ሴኔት ጸድቆ ለዛሬው የምርቃት ቀን መብቃታቸውን ተናግረዋል፡፡

"ተመራቂ ተማሪዎች ኢትዮጵያ እናንተን በጥብቅ ትፈልጋችኋለችና ይህ ደስታ የእናት ሀገራችሁ ጭምር ነው" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ "የሰለጠናችሁበት የተከበረው የሕክምና እና የጤና ሙያዎች ምን ይህል ፈታኝ ግን ፈዋሽ እንደሆነ እንገነዘባለን" ብለዋል፡፡

አክለውም፤ "እንቅልፍ አልባ ለሊቶች፣ ስንፍና እና ድካም የሻረ ትጋት በብዙ ተግዳሮቶች የተፈተነ ግን ያልተሸነፈ ጥንካሬያችሁ ለዛሬው ቀን አብቅቷችኋልና እንኳን ደስ አላችሁ" ሲሉ ለተመራቂ ተማሪዎች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

Post image

የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ዶ/ር ደረጄ ድጉማ በበኩላቸው፤ "ተመራቂዎች አድካሚውን የትምህርት ጉዞ በስኬት አጠናቃችሁ በጉጉት ስትጠብቁት ለነበረው የምርቃት ቀናችሁ እንኳን አደረሳችሁ" ያሉ ሲሆን፤ "ቀጣይ የሀገራችን ጉዞ ዛሬ የምትመረቁት ተማሪዎች እጅ ላይ የሚወድቅ ነው" ብለዋል፡፡

አክለውም ተመራቂ ተማሪዎች የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት እራሳቸውን ማዘጋጀት እንደሚገባቸው በማሳሰብ፤ ተመራቂ ተማሪዎች በቀጣይ ወደ ሥራ ሲገቡ ሙያቸውን ያለ ስስት የሚሰጡ እንዲሆኑም ጠይቀዋል፡፡

Post image

የተማሪዎች የምርቃት ሥነ-ስርዓቱ የተከናወነው፤ የዩኒቨርስቲው 70ኛ ዓመት እና አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል እየተከበረ ባለበት ወቅት መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገውም በመድረኩ ተነግሯል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይም በቅርቡ ሕይወቱ ያለፈውና በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በጠቅላላ ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስት እና የጉበት፣ የቆሽትና የሃሞት መስመር ሰብ ስፔሻሊስት ሃኪምነት የነበረውን ዶ/ር አንዱዓለም ዳኜን በማሰብ የህሊና ጸሎት ተደርጓል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ