የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መንግሥትም ሆነ በክልሉ የሚቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎችን ወደ ድርድር ለማምጣት ነፍጥ ያነገቡ በመሆናቸው፤ ንግግሩን ውስብስብ አድርጎታል ሲል የአማራ ክልል የሰላም ካውንስል ለአሐዱ ገልጿል፡፡

አሐዱም "በ6 ወር ውስጥ ካውንስሉ ምን ሥራዎችን አከናወነ?" ሲል የክልሉን የሰላም ካውንስል ሰብሳቢ አቶ ያየህይራድ በለጠን ጠይቋል፡፡

ሰብሳቢው በሰጡት ምላሽ፤ ሁለት የታጠቁ ሃይሎችን ችግር ለመፍታት የጊዜ ገደብ ማስቀመጥ አስቻይ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡

"ነገር ግን በአንጻራዊ ሁኔታ መንግሥትም ሆነ በክልሉ የሚቀሰቀሱ ታጣቂዎች የሚቀሳቀሱበት ቀጠና ለንግግር የሚያሳዩት ሂደት የሚበረታታ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አክለውም፤ የሲቪል ማኅበራት በሰላሙ ዘርፍ ላይ እያደረጉት ያለው አተዋጽኦ ቀላል እንዳሆነ ገልጸው፤ "ነገር ግን መንግሥት ለድርድሩ ቁርጠኛ ሆኖ እንዲመጣ አሁንም ጫና ማሳደር አለባቸው" ሲሉ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም በአንድም በሌላም መልኩ በጠመንጃ አፈሙዝ ችግርን ለመፍታት መሞከር፤ በዜጎች ላይ እና በሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ማሕበራዊ ጉዳዮች ላይ ቀውስ ከማምጣት የዘለለ ዘላቂ የሆነ መፍታሄ ሊያመጣ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡

"ይህን ችግር ደግሞ በሁለቱም ወገን በውጊያ ላይ የሚገኙ ኃይሎች ከግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው" ሲሉም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

እንዲሁም አሁን ባለው ሁኔታ በኃይል የማይፋታ መሆኑን መንግሥት ከግንዛቤ በመውሰድ፤ የተሻለውን እውነተኛ የሆነ የንግግር አማራጭ እንዲከተል ጠይቀዋል፡፡

ነገር ግን መንግሥት 'የሕግ ማስከበር ዘመቻ' በሚል ወደ ክልሉ የሰላም አስከባሪ ያህል ካስገባ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን፤ አሁንም በክልሉ ከሰላም አኳያ ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉ ተገልጿል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ