መጋቢት 5/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በትግራይ ክልል በጊዚያዊ አስተዳደሩ አመራሮች እና በህወሓት መካካል በተከሰተው መከፋፈል ምክንያት የተፈጠረው ውጥረት እንዳሳሰባቸው፤ አሐዱ ያነጋገራቸው የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በትግራይ ክልል በጊዚያዊ አስተዳደሩ አመራሮች እና በህወሓት መካካል የተፈጠረው ልዩነት እየሰፋ ወደ ግጭት እንደያመራ የብዙዎች ስጋት ሆኗል፡፡

ከሰሞኑም በተለይ ከመቀሌ ቅርብ ርቀት ላይ በአዲ ጉደም ከተማ የፀጥታ ሃይሎች ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ሃይሎች ላይ በወሰዱት የሃይል እርምጃ አራት የሚሆኑ ዜጎች መጎዳታቸው፤ ችግሩ ወደ ወታደራዊ ግጭት እንዳያመራ ስጋት ውስጥ ጥሎታል፡፡

አሐዱም "ይህ ሁኔታ በክልሉ በተለይም በመቀሌ ያለው ሁኔታ ምን ይመስላል? በአመራሮቹ መካካል የተነሳው መከፋፈል የፈጠረው የጦርነት ስጋትስ ምን ይሆን? እንዲሁም በተለይም በዋና ከተማዋ መቀሌ ያለው አሁናዊ በሁኔታ ምን ይመስላል?" ሲል በመቀሌ እና አከባቢው የሚኖሩጨነዋሪዎችን ጠይቋል፡፡

አሐዱ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ሰላም ከምንም በላይ የሚያስቀድሙት ጉዳይ መሆኑን ቢገልጹም፤ በአመራሮቹ መካካል የተፈጠረው ልዩነት በህዝቡ መካከልም የአቋም ልዩነት መፍጠሩን ተናግረዋል፡

ይሁን እንጂ የሁሉም ፍላጎት ሰላም መሆኑን በማንሳት በተለይም ክፍፍሉ በከተማው እንስቃሴ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩን ጠቁመዋል፡፡

በመጀመሪያ ሀሳባቸውን የሰጡት በተለይም የጊዚያዊ አስተዳደሩ የፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቁን የሚፈደግፉ አሐዱ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች፤ "መንግሥት ችግሩን ሊፈታ ይገባል" ሲሉ ስጋታቸው ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከጸጥታው ስጋት በተጨማሪ 'በቀጣይ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ጦርነት በትግራይ ይነሳል' የሚል ስጋት መኖሩን ያነሱት ነዋሪዎቹ፤ በተለይም የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ መጨመር እንዲሁም የመድሃኒት እጦት ከፍተኛ ስጋት እንደፈጠረባቸው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ሀሳብ ተቃራኒ የሆነ አስተያየት ያላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ፤ በአሁን ሰዓት ስጋት የሚሆን ጉዳይ አለመኖሩን በማንሳት "ከተማዋ በተረጋጋ ሁኔታ ላይ ናት" ብለዋል፡፡

በዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካዔል የሚመራው የህወሓት ቡድን በአሁኑ ሰዓት እየወሰደ ያለው እርምጃ፤ 'ሕግን ለማስከበር' በመሆኑ እየተደረገ ያለውን አካሄድ እንደሚደግፉትም ገልጸዋል፡፡

ሆኖም በአመራሮቹ መካካል የተፈጠረው መከፋፈል በርካታ ስጋቶች ሲፈጠሩ የቆዩ ሲሆን፤ ይህ ስጋት ወደ ለየለት ግጭት እንዳይገባ ተፈርቷል፡፡

ይህንንም በሚመከለከት የግዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ፤ "የፌደራል መንግሥት ሕግ እንዲያስከብር" ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አሐዱ ያነጋገራቸው ነዋሪዎችም 'ሰላም ፈላጊዎች' መሆናቸውን በማንሳት መንግሥት የተፈጠረውን ስጋት እንዲያስቆምላቸውና ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲገቡ እንዲደረግም ጠይቀዋል፡፡

በህወሓት እና ጊዚያዊ አስተዳደሩ መካካል ያለው ውጥረት እየተባባሰ ስለምመጣቱ በርካታ ማሳያዎች እየታዩ ሲሆን፤ ትግራይ ዳግም ወደ ግጭት እንዳትገባ ስጋት ፈጥሯል፡፡

በትላትናው ዕለትም በአዲስ አበባ በመገኘት መግለጫ የሰጡት የጊዚያዊ መስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ "መንግሥት ራሱ ያቋቋመውን አስተዳደር የመውደቅ አደጋ ሲያጋጥመው የማንሳት ሃላፊነቱን ይወጣ" ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም የትግራይ ክልልን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መቀመጫቸውን፤ አዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት አቶ ጌታቸው በሰጡት ማብራሪያ፤ "ሕጋዊ ተቀባይነት ያጣው የህወሓት ቡድን ከተወሰኑ የታጣቂ መሪዎች ጋር በመተባበር በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ስልጣን በኃይል ለመንጠቅ እየተንቀሳቀሰ ነው" ብለዋል።

አክለውም፤ "ሕገ-ወጥ ቡድኑ ጊዜያዊ አስተዳደሩን በኃይል ለማፍረስ በፈጠረው ችግር የፕሪቶሪያውን ስምምነት በግልጽ ንዶታል" ያሉ ሲሆን፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የትግራይ ክልልን ወደ ብጥብጥና ትርምስ ያስገባውን ኃይል ለማስቆም አስፈላጊውን ጫና እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ፓርቲ (ሕወሓት) በይፋዊ ማህበራዊ ሚዲያው በትናንትናው ዕለት ባሰራጨው መግለጫ፤ "ማቋረጫ የሌለው ብሄራዊ ክህደት ቀጥሏል" ሲል ወቀሳ ሰንዝሯል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ