የካቲት 10/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤር ባስ ኩባንያ ጋር የሰባት ዓመት ሁለንተናዊ የጥገና አገልግሎቶች ስምምነትን ተፈራርሟል።

በስምምነቱ መሰረት ኩባንያው 24 ለሚሆኑ A350 እንዲሁም A350-900 እና A350-1000 ሞዴል ኤር ባስ አውሮፕላኖች የጥገና አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ነው የተነገረው፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ የኤርባስ ጥገና አቅርቦት እንዲሁም የምህንድስና እና የጥገና ድጋፍ ተጠቃሚ ይሆናል ተብሏል።

የኤርባስ ኩባንያን የምህንድስና እውቀት በመጠቀም አየር መንገዱ የተሻሻለ የአውሮፕላን አካላት አቅርቦት እና የተመቻቹ የጥገና ሂደቶችን እንደሚያገኝ ነው የተነገረው።

እነዚህ ማሻሻያዎች የአውሮፕላኖችን የእረፍት ጊዜ ይቀንሳሉ የተባለ ሲሆን፤ አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የሥራ ቅልጥፍናን እንደሚጨምሩ ተመላክቷል።

Post image

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ኦፊሰር ሬታ መላኩ የስምምነቱን በስምምነቱ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ "የመጀመሪያው የኤ350 ቤተሰብ አፍሪካዊ ኦፕሬተር እንደመሆናችን መጠን፤ በአገራችን ከፍተኛ የአፈጻጸም ደረጃዎችን ለማሳካትና አስተማማኝነትን ለማስጠበቅ ቆርጠን ተነስተናል" ብለዋል፡፡

"በዚህም ስምምነት ከኤርባስ ጋር የረዥም ጊዜ ትብብር ማድረጋችን ከጥገና ጋር የተያያዙ መዘግየቶችን ለመቀነስ እና ተሳፋሪዎቻችን በደህንነት፣ ምቾት እና አገልግሎት ምርጡን ማግኘታቸውን እንዲቀጥሉ ለማድረግ ይረዳናል።" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኤር ባስ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ የደንበኞች አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ላውረን ኔግሬ በበኩላቸው፤ በአጋርነት ስምምነቱ መሰረት አየር መንገዱ ከፍተኛ የሥራ ቅልጥፍናን እንዲያሳካ የሚደግፉ የጥገና መፍትሄዎችን ለማቅረብ ኩባንያቸው ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

"የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ተዓማኒነትን ለማጎልበት እና ለኤ350 አውሮፕላኖችን የጥገና ሥራዎች ለማቀላጠፍ ኃላፊነት በመውሰዳችን ከፍተኛ ኩራት ይሰማናል" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከኤር ባስ ጋር የቆየ ግንኙነት ያለው ሲሆን፤ በ2007 ዓ.ም. ኤ350-900 አውሮፕላንን ወደ ሃገር በማስገባት የመጀመሪያው አፍሪካዊ አየር መንገድ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አየር መንገዱ በያዝነው ዓመት ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው ኤርባስ ኤ350-1000 አውሮፕላን ወደ ሀገር ማስገባቱ ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ