መጋቢት 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አጫጭር ስልጠናዎችን ጨምሮ በመደበኛ የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፎች ውስጥ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች እየሰለጠኑ እንደሚገኝ የፌደራል የቴክኒክ እና ሙያ ኢንስቲትዩት አስታውቋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ብሩክ ከድር በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢዎች የሚሰጡ የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠናዎች 70 ከመቶው የተግባር እና 30 ከመቶው የንድፈ ሀሳብ (ቲዎሪ) እንዲሆኑ መመሪያው እንደሚያዝ የገለጹ ሲሆን፤ "ነገር ግን በሁሉም አካባቢዎች ላይ ይህ እየተተገበረ መሆኑን ምልከታ ማድረግ ይጠይቃል" ብለዋል።
"የቴክኒክ እና ሙያ ስልጠናዎች ግብዓት ሂደት እና ውጤትን የያዙ ናቸው" ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ይህም በሁሉም የሀገሪቱ የስልጠና ማዕከላት የተሟላ ነው ለማለት እንደማይቻል ተናግረዋል።
አክለውም ይህን ለማወቅ እና ያሉትን ክፍተቶች ለማረም የሚያስችል ጥናት ከአንድ ሳምንት በፊት መጀመሩ የተገለጹ ሲሆን፤ ጥናቱ በተለይም በዘርፉ ያሉት ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸውን ለማወቅ የሚረዳ ግብዓት ይገኝበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል።
ሌላኛው ችግር ማህበረሰቡ ለዘርፉ ያለው አመለካከት በሚፈለገው ልክ አለማደግ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ብሩክ፤ "አማራጭ የማጣት ተደርጎ መወሰዱ ለዘርፉ አለማደግ እንደ እንከን የሚነሳ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
የቴክኒክ እና ሙያ ዘርፍ ለሀገር እድገት እና ለእውቀት ሽግግር ከሚያበረክተው አስተዋፅኦ አንፃር ስላልተተገበረ፤ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት በማሳደግ በተግባር እንዲታወቅ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
አሁን ላይ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ "ፖሊሲዎችን ከማሻሻል ባለፈ የቴክኒክ እና ሙያ ካውንስል እንዲቋቋም በማድረግ አሁን ላይ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች አጫጭር ስልጠናዎችን ጨምሮ በዘርፉ እየተማሩ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
አሁንም ግን ዘርፉን የማስተዋወቅ እና ተጠቃሚ የማድረግ አንፃር፤ የሚሰሩ ሥራዎች ላይ ክፍተት እንደሚስተዋል ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች በቴክኒክ እና ሙያ ዘርፎች እየተማሩ እንደሚገኝ ተገለጸ
