ጥር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ ከቱሪዝም ሐብቶቿ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ መገናኛ ብዙኃን መወጣት የሚገባቸውን ሚና አልተወጡም ሲሉ የኦሮሚያ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽኖች ገልጸዋል፡፡

ክልሉ እምቅ የቱሪዝም አቅም እንዳለው ያስታወሱት የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ፤ "መገናኛ ብዙኃን ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጪ ጎብኚዎች ታሪክን፣ ባህልን፣ የተፈጥሮ ሃብትን ያገናዘበ የማስተዋወቅ ሥራ በበቂ ሁኔታ አልሰሩም" ብለዋል፡፡

አክለውም ለዘርፉ መነቃቃት የመገናኛ ብዙኃን ሚና ከፍተኛ በመሆኑ መገናኛ ብዙኃኑ የማስተዋወቅ እና በተለያ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን ለዕይታ የመጋበዝ ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይንቱ መልኩ በበኩላቸው፤ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በርካታ የቱሪዝም መስህቦች ቢኖሩትም በበቂ መጠን ስላልተዋወቀ የሚገባውን ያህል ጎብኚዎችን እያገኘ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጎብኝዎች ኢትዮጵያን ተመራጭ የቱሪስት መዳረሻ እንዲያደርጉ ለተጀመሩ ጥረቶች ሚዲያዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

"ክልሉ ከፍተኛ የቱሪዝም ዓቅም ያለው ነው" ያሉት ኃላፊዋ፤ ይህንን ለመጠቀም የባለ ድርሻ አካላት ትስስር ዘላቂ አለመሆኑ እና የቁርጠኝነት ማነስም ሌላው ችግር እንደሆነ አመላክተዋል።

አክለውም "የክልሎች መንግሥታት ያላቸው ዓቅም ውስን ነው" ያሉ ሲሆን፤ ከግሉ ዘርፍ፣ ለጋሽ ድርጅቶች እና የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ተጨማሪ ጥናት በማድረግ፣ ሥልጠና የመስጠት፣ የማስተዋወቅ ሥራ የቀጣይ ትኩረቶች መሆናቸውን ለአሐዱ ገልጸዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ