ጥር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ሳውዲ አረቢያ ያልተፈቀደ የሃጅ ጉዞን ለመግታት ኢትዮጵያን ጨምሮ ለ14 ሀገራት አዲስ የቪዛ ፖሊሲ ተግባራዊ አድርጋለች፡፡

ሳዑዲ አረቢያ ከፈረንጆቹ የካቲት 1 ጀምሮ ከ14 ሀገራት ለሚመጡ ተጓዦች ቢበዛ ለ30 ቀን ብቻ የሚቆይ ቪዛ መስጠት መጀመሯን ነው የገለጸችው።

ይህ እርምጃ በረጅም ጊዜ የጉብኝት ቪዛ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ያልተፈቀላቸው የሃጅ ተጓዦች ስጋትን ለመፍታት ታስቦ የተወሰደ መሆኑ ተነግሯል።

አዲሱ ደንብ ከአልጄሪያ፣ ባንግላዲሽ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ኢራቅ፣ ዮርዳኖስ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያ፣ ፓኪስታን፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያ እና የመን ተጓዦችን ይመለከታል ተብሏል፡፡

በዚህም መሰረት ከእነዚህ ሀገራት ለቱሪዝም፣ ለንግድ እና ለቤተሰብ ጉብኝት የሚደረገውን የአንድ ዓመት የመግቢያ ቪዛ ላልተወሰነ ጊዜ መታገዱን ሀገሪቱ አስታውቃለች።

በተሻሻለው ሕግ መሰረት፣ ከሀገራቱ የመጡ ጎብኚዎች ለአንድ መግቢያ ቪዛ ብቻ ማመልከት የሚችሉት ለ30 ቀናት ብቻ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ነገር ግን እግዱ የሀጂ፣ ኡምራ፣ የዲፕሎማት እና የመኖሪያ ቪዛን እንደማያካትት ተገልጿል።

የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በሐጅ ጉዞ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርግ ሲሆን፤ ለእያንዳንዱ ሀገር የተወሰነ የሐጅ ኮታን ይመድባል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ ቱሪስቶች እነዚህን ገደቦች በረጅም ጊዜ ቪዛ በማለፍ፤ በሀገሪቱ መጨናነቅ መፍጠራቸው አሳሳቢ ጉዳይ እየሆነ መምጣቱም ተነግሯል።

በፈረንጆቹ 2024 ከ 1 ሺሕ 200 በላይ ምዕመናን በከፍተኛ ሙቀት እና መጨናነቅ ሳቢያ ሲሞቱ፣ ባለሥልጣናቱ ያልተመዘገቡ ምዕመናን ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆናቸውን ተናግረዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ