የካቲት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ የመንገድ አጠቃቀም ሕግን ተላልፈው የተገኙ፤ ከ18 ሺሕ በላይ እግረኞች የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጡ መደረጉን የከተማ አስተዳደሩ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ለአሐዱ አስታውቋል፡፡

በባለስልጣኑ የትራፊክ ቁጥጥርና ትራፊክ አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ አያሌው ኢቲሳ፤ ቅጣቱ የእግረኞችን ደህንነት ለማሻሻል እና በከተማው የሚደርሰውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ ታስቦ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት ቅጣቶች የሚጣሉት ሙሉ የእግረኛ መሠረተ ልማት ባለባቸው አካባቢዎች ብቻ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ይህም ማለት የእግረኛ መንገድ ባለባቸው አካባቢዎች፣ የዜብራ ማቋረጫዎች በግልጽ በሚታዩባቸው እና ምልክት በተደረገባቸው ቦታዎች ላይ ቅጣቶቹ ተፈጻሚ እንደሚደረጉ አብራርተዋል፡፡

ይህም ተግባራዊ የተደረገው የቅጣት አሰራር አሁን ላይ በእግረኞች ላይ እየደረሰ ያለውን የትራፊክ አደጋ ከመቀነስ አንጻር ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ በከተማው ውስጥ 22 ቦታዎች ለእግረኞች ሕግ ማስከበር ቁልፍ ተብለው የተለዩ መኖራቸውንም ዳይሬክተሩ አንስተዋል፡፡

አክለውም እግረኞችን ለቅጣት ከሚዳርጉ ዋነኛ ጥፋቶች መካከል፤ የጆሮ ማዳመጫ አድርጎ ዜብራ ማቋረጥ፣ ለእግረኛ ያልተፈቀዱ ቦታዎች ላይ መቀሳቀስ እና በቀለበት መንገድ ላይ መዝለል ይገኙበታል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች 80 በመቶ የሚሆነው የሞት አደጋ የሚከሰተው በእግረኞች ላይ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የእግረኛ ጥሰት ለትራፊክ አደጋ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በመሆኑም "ሕገ-ወጥ የእግረኛ ባህሪን ለመግታት እና የመንገድ ደህንነትን ለማሻሻል ጥብቅ እርምጃዎች እየተወሰዱ ነው" ብለዋል።

አክለውም፤ እግረኞች የትራፊክ ሕግን በመከተል የከተማውን የትራፊክ ፍሰት ማስተካከል እና እራሳቸውን ከአደጋ መጠበቅ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ ቁጥር 395/ 2009 መሠረት በእግረኞች የሚፈፀሙ ጥፋቶች ላይ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ