የካቲት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጵያ የናይል ተፋሰስ አባል ሀገራት በዓባይ ግድብ ላይ ጉብኝት እንዳያደርጉ አስቀድማ ደብዳቤ መላኳን ተከትሎ፤ ግብፅ ለሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ሚኒስትሮች ጉብኝት እንዳያደርጉ በደብዳቤ ብትጠይቅም አንድም ሀገር እንዳልተቀበላት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ቢሆንም ግን የተደረገው የዓባይ ግድብ ጉብኝት ለሚኒስትሮች ጥያቄ ምላሽ የሰጠ ነው ያሉት ሚንስትሩ፤ "በዓባይ ግድብ ላይ በሚኒስትሮቹ የተካሄደው ጉብኝት በኢትዮጵያ ተቃራኒ የቆመውን አካል ያሽመደመደ ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"እኛ በደብዳቤ ለታጀበው የግብፅ የ"አትጎብኙ" መልዕክት የመልስ ምት አልሰጠንበትም" ያሉት ሚኒስትሩ፤ "ጉዳዩ የተለመደ የሐሰት ፕሮፖጋንዳቸው አካል እንደመሆኑ ንቀን አልፈነዋል" ብለዋል።
ይሄ ደግሞ ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን፣ የተፋሰሱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮችም ምላሽ ሳይሰጡበት ያለፉት ጉዳይ መሆኑንም ገልጸዋል።
አክለውም፤ "የዓባይ ግድብ እንዳይጎበኝ በግብፁ የውሃ ሚኒስትር የቀረበው ጥያቄ ትርጉሙ ለሌሎች የተፋሰሱ ሀገሮች ያላቸውን ንቀት ማሳያ ነው" ብለዋል፡፡
"ምክንያቱም ኢትዮጵያ ግድቧን ለማስጎብኘት መጋበዝ መብቷ እንደሆነ ሁሉ፤ እነርሱም የኢትዮጵያን ግብዣ መቀበል አለመቀበል መብታቸው ነው" ሲሉም ሚኒስትሩ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ "በመጀመሪያም ቢሆን የዓባይ ግድብን እንዲጎበኝ የጋበዘችው ኢትዮጵያ እንጂ የናይል ቤዚን ኢንሼቲቭ አይደለም" ያሉት ሚኒስትሩ፤ የግብፁ የውሃ ሚኒስትር የአትጎብኙ መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉም አንድም ሀገር እንዳልተቀበላቸው ተናግረዋል።

"ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ትልቅ ስኬት ነው። ግብፅም በኢትዮጵያ ሜዳ ለመጫወት ፈልጋ በራሷ ላይ ግብ አስቆጥራለች፤ ይሄም የአደባባይ ምስጢር ለመሆን ችሏል" ብለዋል። "ይሄ ደግሞ ለግብፅ አላስፈላጊ ጥይት ተኩሳ እራሷን እንደማቁሰል የሚቆጠር ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
ወደ ናይል ቀን ስብሰባ የመጡት የተፋሰሱ አባል ሀገራት በሙሉ የዓባይ ግድብን በሚኒስትር ደረጃ ጉብኝቱን ማድረጋቸውን የገለጹም ሲሆን፤ በጉብኝቱም ሁሉም ለነበራቸው ጥያቄ ምላሽ አግኝተውበታል ብለዋል።
ሚኒስትሮቹ ዓባይ ግድብ ከደረሱ በኋላ የነበራቸው አግራሞት በግልጽ የሚታይ ነበር ያሉት ሚኒስትሩ፤ ቀደም ሲል ሲነዛ የነበረው ፕሮፓጋንዳ እና መሬት ላይ ያዩት እውነታ ልዩነቱ አስደንቋቸዋል ብለዋል።
ጎብኚዎቹ ግድቡን ገና እንዳዩት ከመደነቃቸው ባለፈ፣ ግብፆች ሲያራግቡት የነበረው ፕሮፓጋንዳ ሐሰት መሆኑን ተገንዝበዋል።
ጉብኝቱ፣ በተለይ ግብፅ ለሌላ ጊዜ የምትናገረውን ንግግር አስባበት እንድትናገር ያደረገ ጭምር ነው ብለዋል።
ቀደም ሲል እንዲጎበኙ ታስበው የነበሩ ሃያ ሰዎች ቢሆኑም፤ ከግብፁ ሚኒስትር የአትጎብኙ ጥሪ በኋላ የሰው ቁጥር ወደ 30 ከፍ ማለቱም ለጉብኝቱ ከፍ ያለ ትኩረት የሰጡት መሆኑን የሚያመላክት መሆኑን አመላክተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ