የካቲት 4/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ያለ አግባብ ዋጋ በጨመሩ፣ ምርት በደበቁና ከተሰጣቸው ንግድ ፈቃድ ውጭ ሲሰሩ የተገኙ እና በሌሎች ሕገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ከተገኙ ነጋዴዎች ውስጥ 14 ሺሕ 129 የንግድ ተቋማት ዳግም ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጉን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ለአሐዱ አስታውቋል።
የቢሮው የንግድ ተቆጣጣሪ ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ቅድሥት ስጦታው የመግባቢያ ስምምነት ተደርጎ ተቋማቱ ወደ ሥራ እንዲመለሱ መደረጉን እና የተለየ ክትትል እንደሚደረግባቸው ተናግረዋል፡፡
ከ17 ሺሕ የንግድ ተቋማት ውስጥ 14 ሺሕ 129 የሚሆኑት መመለሳቸውን የተናገሩት ኃላፊዋ፤ ዳግም በዚህ ድርጊት ላይ ተሰማርተው ከተገኙ በወንጀል ተጠያቂ እንደሚደረጉም አንስተዋል፡፡
ከቀበሌ ጀምሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቷቸው ቀሪዎቹም በድጋሚ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለማድረግ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
ኃላፊዋ አያይዘውም የእርምት እርምጃዎች ተግባራዊ መደረጉ የምርት፣ የአቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት መንግሥት ማግኘት ያለበትን ገቢ እንዳያጣ አስተዋጾ እንዳለው አንስተው፤ መሰል ሥራዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በመዲናዋ ዳግም ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተደረጉ ከ14 ሺሕ በላይ የንግድ ተቋማት የተለየ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ ተገለጸ
