የካቲት 4/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በኢትዮጵያ የመንግሥትም ይሁን የግል ተቋማት በምርት እና በአገልግሎት ለውጥ እንዲያመጡ ለማስቻል የምርት እና የአገልግሎት ግምገማ በማድረግ የሚሰጠውን የጥራት ሽልማት በገንዘብ የሚቸረችሩ ተቋማት መኖራቸው፤ የኢትዮጵያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የሚሰራውን ሥራ ዋጋ እያሳጡት መሆኑ ተገልጿል፡፡
የድርጅቱ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ መብራት "የሀሰተኛ ሽልማት ጉዳይ እንደ ቢዝነስ የተያዘ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካልት ሊፈቱት ይገባል" ብለዋል፡፡

አንዳንድ ተቋማት እንደ ችግር ብለው በለዩዋቸው ጉዳዮች ሳይቀር 'እንሸልማችሁ' የሚል ደብዳቤ ተሰጥቷቸው እንደነበር ወደ ተቋሙ ያቀረቡ ድርጅቶች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም 'የሽልማት መጠኑ ቀንሷል' እና 'ጨምሯል' ማለት ባይቻልም ተቋማቱ አሁንም ሕገወጥ ሥራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
አክለውም "በትክክለኛው መንገድ ተመዝነው ብቁ የሆኑ ድርጅቶች እንዲኖሩ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ቁጥጥር በማድረግ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል" ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት፤ ለጥራት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ የሽልማት ስርዓት በመዘርጋት የሀገሪቱን ዓለም አቀፍ የተወዳዳሪነት ብቃት ማሳደግ እና የጥራት ጽንሰ ሐሳብን በማስረጽ ጥራት የሀገሪቱ ባህል እንዲሆን የማገዝ አላማን ይዞ በ2000 ዓ.ም የተቋቋመ ድርጅት ነው
ድርጅት ባለፉት ጊዜያት 11 የጥራት ሽልማት ውድድሮች ያከናወነ ሲሆን፤ በእነዚህም ውድድሮች ላይ 502 ድርጅቶችና ተቋማት ተሳትፈዋል፡፡
በቀጣይም ለሚያከናውነው ለ12ተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ውድድር እስከ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ ምዝገባ በማካሄድ ላይ ይገኛል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ