ጥር 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የክልል ከተሞች በቅንጅት በመሆን የአፈር ማዳበሪያ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንዲያስተካክሉ በማድረግና በየክልሉ ባለው የፀጥታ መዋቅር መሰረት የማስተካከያ እርምጃን በመስጠት፤ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ አካላት ላይ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከበደ ላቀው ለአሐዱ፤ አጠቃላይ በ2017/2018 ወደ 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዢ በእቅድ ተይዟል።
በተጨማሪም ከባለፈው ዓመት የዞረ 3 ሚሊዩን ኩንታል አሁን ላለው የበጋ መስኖ እና የአትክልትና ፍራፍሬ ሥራዎች በተጨማሪም ከ2 ሚሊዩን በላይ ኩንታል ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መሆኑን አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ያለው የአፈር ማዳበሪያ በታቀደለት ጊዜ ተደራሽ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
አሐዱም ከሰሞኑ በሲዳማ ክልል የተከሰተውን የአፈር የማዳበሪያ ዋጋ መናር መነሻ በማድረግ፤ "አሁን ላይ እንደ ሀገር በምን ያክል ዋጋ እየተሸጠ እንደሚገኝና ወደፊትስ የሚኖረው የዋጋ መጠን ምን ይመስላል?" ሲል ጠይቋል።
የሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚው እንደ ግብርና ሚኒስቴር አሁን ላይ እየሰሩበት ያሉት አቅርቦትን በተመለከተ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ለጊዜው እየቀረበ ስላለው የዋጋ ጭማሪ መረጃው እንደሌላቸውና በቀጣይ እንደሚገለጽ ጠቁመዋል።
በመሆኑም ያለአግባብ ሕገወጥ ሥራዎችን በሚሰሩና ዋጋን በሚጨምሩ አካላት ላይ ግን ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያደርግ አፅንኦት በመስጠት፤ "መንግሥት ከፍተኛ በጀት መድቦበት ወደ ሀገር ውስጥ እየገባ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ መሉ ለሙሉ ለአርሶአደሩ ተደራሽ እንዲሆን የማድረግ ሥራ በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ
