ጥር 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የኡጋንዳ ፖሊስ ከማዕከላዊ ባንክ የኤሌክትሮኒክስ ሲስተም በመጥለፍ 62 ቢሊዮን ሽልንግ ወይንም 16 ነጥብ 87 ሚሊዮን ዶላር በመመዝበር የጠረጠራቸውን 9 የገንዘብ ሚኒስቴር ባለስልጣናት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።
በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ያሉ የሂሳብ ሹም ቢሮ ኃላፊዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት የወንጀል ምርመራ ዲፓርትመንት ምርመራውን ለማቀላጠፍ ባቀረበው ጥሪ መሰረት መሆኑን፤ የሀገሪቱ የግምጃ ቤት ፀሐፊ ራማታን ግጎቢ በሰጡት መግለጫው መናገራቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል።
"በግምጃ ቤት ውስጥ አንዳንድ ሥራዎችን በሚመለከት በመካሄድ ላይ ባሉ ምርመራዎች ምክንያት፤ ከሂሳብ ሹም ጄኔራል ጽሕፈት ቤት ጋር ግንኙነት ያላቸው አንዳንድ መኮንኖች በወንጀል ምርመራ ክፍል ተጠርተው ተይዘዋል" ሲል የኡጋንዳ ገንዘብ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ላይ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ባለስልጣናት መካከል በሚኒስቴሩ የግምጃ ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አካውንታንት ጄኔራል ላውረንስ ሴማኩላን እንደሚገኙበት የተገለጸ ሲሆን፤ የጽ/ቤት ኃላፊው ምርመራዎቹን ለማጠናቀቅ በወንጀል ምርመራ ክፍል በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሯል፡፡
በአውሮፓውያኑ ሕዳር ወር 2024 ጠላፊዎች የግምጃ ቤቱን ስርዓት በመስበር ከ60 ቢሊዮን ሽልንግ በላይ ኪሳራን ማድረሳቸውን ተከትሎ የተለያዩ የምርመራ ሪፖርቶች ወጥተዋል፡፡ ይህንንም የሚያጣራው የወንጀል ምርመራ ዲፓርትመንት ሥራውን ጀምሯል።
በወቅቱም የሀገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ሄንሪ ሙሳሲዚ ጠላፊዎች በሕገ-ወጥ መንገድ ስርዓቱን ማግኘት እንደቻሉ ቢናገሩም፤ ተመዝብሯል ያሉት ገንዘብ ሪፖርት ከተደረገው ያነሰ መሆኑን የዩጋንዳ ፓርላማ አስታውቋል፡፡
በታሕሳስ ወር ከጠፋው 16 ነጥብ 87 ሚሊዮን ዶላር ውስጥ፤ 14 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማግኘቱን የኡጋንዳ ባንክ ተናግሯል።
ከሀገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ ገንዘቡ መመዝበሩን ተከትሎ የዓለም ባንክ ዓለም አቀፍ ልማት ማህበር (አይዲኤ)ን ጨምሮ የአፍሪካ ልማት ባንክ የአፍሪካ ልማት ፈንድ (ኤኤፍዲ) እንዲሁም ሌሎች የገንዘብ ተቋማት በኡጋንዳ የነበራቸውን የባንክ አካውንት በመዝጋት ገንዘባቸውን ወደ ሌሎች ሀገራት የባንክ አካውንቶች ማዘዋወራቸው ተነግሯል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኡጋንዳ በሳይበር ጥቃት የተጠረጠሩ 9 የገንዘብ ሚኒስቴር ባለስልጣናትን በቁጥጥር ሥር አዋለች
