መጋቢት 8/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በቅርቡ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲዎች 'ለዘላቂ ሰላም ይበጃል' በማለት ለመንግሥት ያቀረቡትን የሽግግር መንግሥት ምስረታ ምክረ-ሀሳብ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እንደማይቀበለው የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ቀጀላ መርዳሳ ገልጸዋል፡፡
ፓርቲዎቹ ከጋራ ጉባኤያቸው በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ የሽግግር መንግሥት ምስረታ ምክረ ሀሳብ ማቅረባቸው መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱ ይታወቃል።
በሀሳቡ ላይ አስተያየት የሰጡት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ምክትል ሊቀ መንበር ቀጀላ መርዳሳ፤ "የፓርቲ አቋምን የሚገልጹ ውሳኔዎች ከአባላት እውቅና ውጪ መተግበር የለባቸውም" ብለዋል።
እንደዚህ ዓይነት ፖለቲካዊ ውሳኔ ሲወሰን ቢያንስ የፓርቲውን ሁለት ሦስተኛ አባላት ድምጽ ማግኘት ነበረበት የሚሉት አቶ ቀጀላ፤ የሽግግር መንግሥት ምስረታ ትልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን በማንሳት "ውሳኔው የተነገረው ምልዐተ ጉባኤውን አሟልቶ እውቅና ተሰጥቶት አይደለም" ብለዋል።
"በኦሮሚያ ነጻነት ግንባር ሥም ኦሮሚያ ላይ 'የሽግግር መንግሥት መሰርቻለሁ' የሚባል ከሆነ ድርጊቱም፣ ሐሳቡም ከፓርቲው እውቅና ውጪ ነው" ብለዋል።
አክለውም እንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎች በዋና ሥራ አስፈጻሚ በኩል ብቻ ሳይሆን፤ በጠቅላላ ጉባኤው ሊወሰኑ የሚገባቸው ስለመሆናቸው አጽንኦት ሰጥተውበታል።
በሌላ በኩል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የትግል እድሜውን ያህል ጠንካራ ፓርቲ መሆን ያልቻለው፤ በውስጥ የስልጣን ሽኩቻ እና ዲሞክራሲያዊ ባለመሆን እንደሆነ አቶ ቀጀላ ተናግረዋል።
አክለውም፤ "የስልጣን ሽኩቻን በመጥላት ጠንካራ አመራሮች ድርጅቱን መልቀቃቸው እና የአመራሮች መገደል እንዲሁም የዲሞክራሲያዊ አሰራሮች መጓደል ለድርጅቱ መዳከም ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው" ብለዋል።
ድርጅቱ ቀደም ሲል የነበረውን የጠንካራ አስተዳደር ቁመና እና ጥንካሬ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስለመዳከሙ አንስተው፤ ለዚህም የውስጥ መከፋፈልና የልዩነቶች መስፋት ተጠቃሽ ሰበቦች ስለመሆናቸው ነግረውናል።
"ልዩነቶቹ እንዲባባሱ የበጀት እጥረት፣ ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖሩ አስተዋጽኦ አድርጓል" የሚሉት ፖለቲከኛው፤ "ፍትሀዊ የስልጣን ሽግግር ቢኖር ድርጅቱ አሁን ያለበት ነባራዊ ሁኔታ ላይ አይገኝም ነበር"ብለዋል።
የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ቀጀላ መርዳሳ ከ #አሐዱ_መድረክ ጋር ያደረጉትን ቆይታ ለመከታተል ከሥር ያሉትን ማስፈንጠሪያዎች ይጠቀሙ!👇
ክፍል አንድ👉 https://youtu.be/79S6Ra_0aAE?si=E7DA5_oRX7p9uBUt
ክፍል ሁለት👉 https://youtu.be/RlAqu8Bmp6M?si=mlLSGAK8C85sdhlU
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ኦነግ የሽግግር መንግሥት ምስረታ ምክረ-ሀሳቡን እንደማይቀበለው የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ
የስልጣን ሽኩቻ እና ዲሞክራሲያዊ አለመሆን ፓርቲው በሚፈለገው ልክ ጠንካራ እንዳይሆን አድርጎታል ብለዋል
