ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ የሰፈረውን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የቀድሞ ይዘታውን ሳይለቅ እድሳት ለማድረግ የተጀመረው ጥናት፤ በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት መቋረጡን የላሊበላ ከተማ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም ጽህፈት ቤት ለአሐዱ ገልጿል፡፡
"የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ላለፉት 15 ዓመታት ያገለገለውን መጠለያ ማንሳት ወይም ማደስ ያልተቻለው ለምንድን ነው? ቅርሱንስ ስጋት ላይ ሊጥል አይችልም?" ወይ ሲል አሐዱ የጽ/ቤቱን የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ልማት ቡድን ተጠሪ አቶ ማንደፍሮ ታደሰን ጠይቋል፡፡
አቶ ማንደፍሮ በምላሻቸው "በዓለም ባንክ ድጋፍ በጊዜያዊነት ከላይ ተሰርቶ የነበረው መጠለያ ለምን ያክል ጊዜ ያገለግላል የሚለው ጥናት ስላልተደረገበት፤ ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት በማህበረሰቡ ዘንድ ቅርሱን ይጎዳዋል የሚል ስጋትን ተፈጥሯል" ብለዋል፡፡
ሁለተኛውን እድሳት ለማድረግ የተጠኑት 7 ጥናቶች ለዩኒስኮ ቢቀርቡም፤ ሁለቱን ጥናቶች ውድቅ በማድረጉ እና እንደገና እንዲጠኑ በማዘዙ ፕሮጀክቱ እንደዘገየም ገልጸዋል፡፡
"50 የሚሆኑ ባለሙያዎች ተሳተፉበት ጥናቱ ቤተ ጊዮርጊስን ብቻ ለራሱ አድርጎ ሌሎቹን አምስት እና ስድስት በአንድ ላይ የሚሸፍን ንድፍ ነው" ያሉት አቶ ማንድፍሮ፤ ነገር ግን ዩኒስኮ በሁለት ጥናቶች ላይ ጥያቄ ማንሳቱን ተናግረዋል፡፡
በፈረንሳይ መንግሥት በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ዕድሳቱ እንደሚከናወን አስታውሰውም፤ እንደገና ጥናቱን ለማካሄድ የፈረንሳይ መንግሥት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ጥናት የሚያደርጉ ባለሙያዎቹን ወደ ቦታው እንዳይገቡ መከልከሉን አስረድተዋል፡፡
በዚህም አሁን ላይ በክልሉ ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ላሊበላን ለማደስ የሚደረገው ጥናት መቋረጡን ተናግረዋል፡፡
ሥራው መቼ ይጀመራል የሚለው ጉዳይ እንዳልታወቀም ነው ጨምረው የገለጹት፡፡
ከዚህ ቀደም የሰሜን ወሎ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ፤ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የጀመሪያው ዙር ጥገና በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንና የሁለተኛው ዙር ጥገና እና ዕድሳት ደግሞ በሚቀጥለው ዓመት እንደሚጀመር ለአሐዱ መግለጹ ይታወሳል፡፡
ለዚህም በሁለተኛው ዙር ለሚደረገው ጥገና እና እድሳት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዩሮ መመደቡን በማንሳት፤ ከጥገና ሂደቱ ጋር በተያያዘ ከ5 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ እድል መፈጠሩንም አስታውቋል፡፡
ቅርሶች በተፈጥሮአዊ እና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጋላጭ በመሆናቸው አስፈላጊውን ጥበቃ እና እክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው በዘርፉ ላይ የሚንቀሳቀሱ ተቋማት ሲገልጽ ይደመጣል፡፡