ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) መቀመጫውን በዮናይትድ ስቴትስ ኖርዝ ኬሮላይና ያደረገው "አይፓስ ኢትዮጵያ" የተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት የሥነ ተዋልዶ ጤና መረጃዎችን በኢትዮጵያ ለሚገኙ አምስት ክልሎች ለማዳረስ ያቀደ የሰባት ዓመታት ፕሮጀክት የማስጀመሪያ መርሀግብር አከናውኗል።
አይፓስ ኢትዮጵያ በሥነ ተዋልዶ ጤና ዙሪያ በአውሮፕያኑ ከ2000 ጀምሮ ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በመሆን ትኩረቱን ያልተፈለገ እርግዝና እና ደህንነቱ ያልተጠበቀ ውርጃ መከላከልን፣ የስነ ተዋልዶ ጤናን ለወጣቶች እና ለአካል ጉዳተኞች ማድረስን እንዲሁም ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን መከላከል እና ተጎጂዎችን በማገዝ ሲሰራ የቆየ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም መሆኑ ይታወቃል።
በፕሮጀክት ማስጀመሪያው ላይ ንግግር ያደረጉት የአይፓስ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ደመቀ ደስታ፤ ፕሮጀክቱ በአምስት የኢትዮጵያ ክልሎች እንደሚሰጥ የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም በአማራ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች የሥነ ተዋልዶ ጤና እና የመረጃ አገልግሎት ተግባራዊ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በአምስቱ ክልሎች ለሚሰጠዉ አገልግሎት ማስጀመሪያ ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ በካናዳ መንግሥት የካናዳ ዓለም አቀፍ ትብብር (GAC) የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግም ዳይሬክተሩ ጨምረዉ ገልጸዋል።
ይህ ለሚቀጥሉት ሰባት አመታት በአጠቃላይ ከስድስት ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት የማስጀመሪያ መርሀ ግብር፤ የጤና ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ እንዲሁም በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ጆሽዋ ታባህንን ጨምሮ በርካታ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት እና አመራሮች በተገኙበት እየተካሄደ ይገኛል።