ጥር 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ኢትዮጽያ ለነዳጅ ግዥ ከዚህ ቀደም በዓመት 4 ነጥብ 5 ቢለየን ዶላር ታወጣ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ላይ ይህ ወጪ በ500 ሚሊየን ዶላር ከፍ ብሎ በዓመት ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደምታወጣ የነዳጅ እና ኢነርጅ ባለስልጣን አስታውቋል፡፡

የባለስልጣኑ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዲባራ ፉፋ "ሁሉም ተሽከርካሪዎቿ ነዳጅን የሚጠቀሙባት ኢትዮጵያ፤ በተለይም የኤሌክትሪክ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማትም ሕይወትን ለማዳን ነዳጅ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው" ብለዋል፡፡

"ሆኖም ይህ ከፍተኛ ወጪ የሚወጣበት ነዳጅ በሕገ-ወጥ ግብይት እና ዝውውር እየተፈተነ ነው" ያሉም ሲሆን፤ በዚህ ሥራ ላይ ዋና ተዋናይ የሆኑት አካላት ሕገ-ወጥነትን ሊከላከሉ እና የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ከሰሞኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በቤንሻንጉል እና በትግራይ ክልሎች ከፍተኛ መጠን ያለው ሕገ-ወጥ ነዳጅ ሲንቀሳቀስ መያዙ ይታወሳል፡፡

ለዚህ ችግር መከሰት አንዱ ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡ ማደያዎች መበራከታቸው እንደሆነ ይገለጻል፡፡

"በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ እና አገልግሎት እየሰጡ ያልሆኑ ማደያዎች በተለይም በድንበር አካባቢዎች ያሉትን ሕገ-ወጥ የነዳጅ ሽያጭ እንዳይከናወንባቸው ከማድረግ አኳራ ምን ተሰራ?" ሲል፤ አሐዱ የባለስልጣኑን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዲባራ ፉፋን ጠይቋል።

ምክትል ዳይሬክተሩ ከማደያዎች ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮችን ማስቀረት ባይቻልም፤ ለመቀነስ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ በተለይም በክልሎች አካባቢ ግብይታቸውን በዲጂታል ያላካሄዱ እና ሕገ-ወጥ የነዳጅ ግብይት ላይ የተሳተፉ ማደያዎች መታሸጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ተገንብተው አገልግሎት ያልጀመሩ፣ በግንባታ ሂደት ላይ ያሉ እንዲሁም የማደያ ቁጥራቸው ካላቸው የተሽከርካሪ ብዛት ጋር ያልመጣጠነ እንደ አዲስ አበባ እና ሸገር ከተሞች ላይ፤ አዳዲስ ማደያዎችን ለመገንባት እና ያሉትንም አገልግሎት ለማስጀመር ጥናት ተሰርቶ ለሚመለከተው አካል መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ በሚገኘው የኮሪደር ልማት ምክንያት፤ ስምንት ያክል ማደያዎች መፍረሳቸውን አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ የሚታወስ ነው።

'ማደያዎቹ ተለዋጭ ቦታ ተሰጥቷቸው ተመልሰው ይገነባሉ' ተብሎ የነበረ ሲሆን፤ እስካሁን ያለውን የግንባታ ሂደት አስመልክቶ አሐዱ ላቀረበው ጥያቄ ምክትል ዳይሬክተሩ ማደያዎቹን ለመገንባት በጥናት ላይ መሆኑን ተናግረዋል።


#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ