ጥር 6/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በመፃኢው ዘመን የምልክት ቋንቋ በማስፋት መስማት ለተሳናቸዉ ዜጎች የሚገጥማቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት የሚያስችል አሰራር መዘርጋት እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በአፍሪካ የመጀመሪያው 15ኛዉ ዓለም-ዓቀፍ የምልክት ቋንቋ ጥናትና ምርምር ጉባኤ፤ “የምልክት ቋንቋን መጠቀም ለመፃዒው ዘምን፤ መፃኢው ዘመንን ምልክት ቋንቋን በመጠቀም”/Using Sign language is the future; the future is using sign language” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

ጉባዔው በዓለም-አቀፍ ደረጃ በየ3 ዓመቱ በተለያዩ የዓለም ሀገራት ሲካሄድ የቆየ ሲሆን፤ በአፍሪካም ሆነ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋራ ትብብር መዘጋጀቱ ተነግሯል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ 5 ሚሊዮን መስማት የተሳናቸው ዜጎች መኖራቸውን የገለጹት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒሰቴር ኤርጎጌ ተስፋዬ፤ ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ መዘጋጀቱ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።

Post image

በጉባዔው ሕግ አውጪዎች፣ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች፣ መስማት የተሳናቸው ምሁራንና ተማራዎችን ጨምሮ ከ600 በላይ ተሳታፊዎች በአካል በመገኘትና በበይነ መረብ መሳተፋቸውን የገለጹም ሲሆን፤ ጉባኤው ከዛሬ ጥር 6 እስከ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለውም የጉባኤው ዋና አላማ መስማት የተሳናቸዉና የምልክት ቋንቋ ተናጋሪዎች ያለባቸውን ተግዳሮቶች ለመፍታት የሚያስችል ቋንቋ መዘርጋት መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህንን በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደዉን የምልክት ቋንቋ ተግባራዊ ለማድረግ በመጺዉ ዘመን የምርምር ሥራዎች እንዲሁም ጥናቶች እንደሚሰሩ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ የሀገር ገጽታንም የሚገነባ በመሆኑ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ኢትዮጵያ የምልክት ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰቦችን ስርዓተ ትምህርት መቅረጽን ጨምሮ፤ በተለያዩ የሕዝብ መገልገያ ዘርፎች ላይ አካታች የሆነ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና ስትጫወት መቆየቷንም አንስተዋል።

Post image

አክለውም በቀጣይም የምልክት ቋንቋ ትምህርትና የትርጉም አገልግሎት ተደራሽነትን ማስፋፋት እንዲሁም፤ ፖሊሲዎችና ትግበራቸው አካታችነትንና እኩልነት የሚያንፀባርቁ እንዲሆኑ በቁርጠኝነት መስራት እነሰደሚገባ አሳስበዋል።

ጉባዔ መስማት የተሳናቸዉ ዜጎችን እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና የምልክት ቋንቋን በማስፋት ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታት ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተገልጿል።