ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የተጀመሩ የመቄዶንያ የአዕምሮ ሕሙማንና አረጋውያን መጠለያ እንዲሁም ለሕሙማን መታከሚያና እንክብካቤ መስጫ የሚሆነውን ሆስፒታል ሕንጻዎችን ለመጨረስ የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ሊካሄድ መሆኑ ተገልጿል
የበጎ አድራጎት ማኅበሩ መስራችና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ቢንያም በለጠ ለአሐዱ እንደተናገሩት፤ ለዚህ ሥራ በሚሆነው የገቢ ማሰባሰቢያ ሂደት ውስጥ እስከ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ እቅድ ተይዟል።
በመቄዶንያ መጠለያ የሚገኙ ሰዎች አብዛኞቹ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው በመሆናቸው ቶሎ ቶሎ ወደ ሕክምና መሄድ ስላለባቸው በዛ ምክንያት የነበረውን ችግር ለመፍታት የሚገነባውን ሆስፒታል እስከ አንድ ሺሕ 200 የሚደርሱ አልጋዎች ያሉትና ባለሙያዎቹንና መሳሪያዎችን ያሟላ እንደሚሆን አክለዋል።
የተጀመረውን ሕንጻ ለመጨረስ ችግር እንደነበር የገለጹት ዶክተር ቢንያም፤ ይህ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ችግሩን ለመቅረፍ ሊያግዛቸው እንደሚችል ተናግረዋል።
መቄዶንያ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ከ44 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍቶ ጧሪ ቀባሪ ያጡ አረጋውያንን እና የአዕምሮ ሕመምተኞችን በማሰባሰብ የበጎ አድራጎት ሥራ እየሰራ የሚገኝ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከ10 ሺሕ በላይ በማዕከሉ የተጠለሉ ዜጎች መኖራቸው ተገልጿል።
ከ2 ሺሕ በላይ የሚሆኑትን የአዕምሮ ሕሙማን በማስታመም ላይ እንደሚገኝና በቀን እስከ አስር የሚደርስ ሰው ወደ ማዕከሉ ለመጠለል እንደሚገባም ተመላክቷል፡፡
በቀጣይም እስከ 20 ሺሕ የሚደርሱ ሰዎችን ለመቀበል እቅድ እንዳለው የዶክተር ቢንያም በለጠ ለአሐዱ አስታውቀዋል።
ለዚህ በጎ ተግባር ክንውን የሚረዳውን ገንዘብ ለማሰባሰብ ልዩ ፕሮግራም የካቲት 1 ቀን 2017 ዓ.ም. ማዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሩ በዋናነት በሰይፉ ፋንታሁን ዩቱብ ቻናል ላይ የሚካሄድ ሲሆን፤ የተለያዩ መንግሥታዊ እና ሃይማኖታዊ ተቋማት እንዲሁም በሀገር ውስጥ እና በውጪ ሀገራት የሚገኖሩ ግለሰቦች ተቋሙን በማገዝ ረገድ በዕለቱ የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
በድጋፍ መርሃ ግብሩ ላይ ድጋፍ ማድረግ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያዊያን በማኅበሩ አድራሻዎች በመደወል እንዲሁም በሁሉም የባንክ አካውንቶች 7979 ገቢ ማድረግ እንደሚቻል ተገልጿል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ