ጥር 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የጸጥታ ስጋት፣ በመንገድ ወሰን ክልል ውስጥ የውኃ እና መብራት መሠረተ-ልማቶች እንዲሁም፤ ንብረቶች በወቅቱ አለመነሳት በሥራው ላይ ፈተና እየሆነበት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር አስታውቋል።
ለፕሮጀክቶቹ መጓተትና መቋረጥ፤ የጸጥታ ችግር፣ የካሳ ክፍያ፣ ወቅታዊ የውጭ ምንዛሬ እጥረት፣ እና የግብዓት አቅርቦት በተለይ ሲሚንቶ፣ ነዳጅና የመሳሰሉት መንገዶች አስተዳደሩን እየፈተኑ መሆናቸው የአስተዳደሩ ሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አስራት አሰሌ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ቡድን መሪው አክለውም፤ የፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ውጤታማ እንዲሆን ከፌደራል እስከ ታችኛው እርከን የሚገኝ የመንግሥት መዋቅር እንዲሁም ወሳኝ የሚባሉት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በአግባቡ አለመወጣታቸው ሌላኛው ፈተና መሆኑን አንስተዋል።
"የክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮች ለካሳ ክፍያ እና ሌሎች ሥራዎች በቅንጅት ከመስራት አንፃር ፍላጎት አለመኖር ከሚነሱ እክሎች ውስጥ ይመደባል" ሲሉም ተናግረዋል።
መንገዶች በአገልግሎት ብዛት በመጎዳታቸው እና ለትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ ባለመሆናቸው ጥገና ለማድረግ እና ለማስፋፋት፣ አዳዲስ መንገዶች እንዳይገነቡ የተጠቀሱ ችግሮች ተቋሙን እየፈተኑ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ እንዲቻል በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑንም ቡድን መሪው በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡
እነዚህን ተግዳሮቶች ጊዜ ሳይሰጣቸው በወቅቱ ለመፍታት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እንዲፈታትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ቡድን መሪው አያይዘውም 'ተግዳሮት ናቸው' ተብለው የተነሱ ጉዳዮችን በሚመለከት እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር በሚያስፈልጉበት ድጋፍ ሁሉ እንዲደርግ ውይይት መደረጉን አንስተዋል፡፡
ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆኑ፤ አሁንም ያልተፈቱ የወሰን ማስከበር ችግሮች በመኖራቸው በየአካባቢው የሚገኙ የመንግሥት አካላት፣ የከተሞች ነዋሪዎች አስፋላጊውን ትብብር እንዲያደርጉም ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ