ጥር 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በጉጂ ዞን ማዕድን በማውጣት ላይ ሥራ ላይ እያሉ ሕይወታቸው ያለፈ የ8 ሰዎች አስክሬን ሙሉ በሙሉ ተገኝቶ ቤተሰቦቻቸው እስኪገኙ በመንግሥት እጅ እንደሚገኝ የጉጂ ዞን ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ለአሐዱ ተገልጿል።

በዞኑ ሰባ ቦሩ ወረዳ ቃቲቻ ቀበሌ በትናንትው ዕለት በባሕላዊ መንገድ ማዕድን በማውጣት ላይ የነበሩ ስምንት ሰዎች በአፈር መደርመስ አደጋ ሕይወታቸው አልፏል፡፡

የዞኑ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አሸናፊ ዳንቆ አደጋው በትናንትናው ዕለት ከ9፡00 አካባቢ መከሰቱን የገለጹ ሲሆን፤ የሟቾች አስክሬን በሙሉ በዛሬው ዕለት መገኘቱን ተናግረዋል።

"አሁን ላይ ወዳጅ ቤተሰብ ተፈልጎ እስኪገኝ ድረስ አስክሬናቸው በመንግሥት እጅ ላይ ይገኛል" ሲሉም ለአሐዱ ገልጸዋል።

Post image

የአደጋው በባሕላዊ መንገድ በተከለከለ ሥፍራ ማዕድን ማውጣት ላይ በተሰማሩ ሰዎች ላይ አፈር በመደርመሱ የደረሰ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በአከባቢው በርካታ በባሕላዊ መንገድ ማዕድን ማውጣት ሥራ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች አልፎ አልፎ በሚከሰት አደጋ ሕይወታቸውን እንደሚያጡም ኃላፊው ጨምምረው አስታውሰዋል።

ከ8 ሰዎች ሕይወት ማለፍ ውጭ ሌላ አደጋ የደረሰበት ግለሰብም ሆነ ንብረት እንዲሁም፤ በአደጋው ከቀያቸው የተናፈቀሉ ነዋሪዎች አለመኖራቸውን ነግረውናል።

ማዕድን በባሕላዊ መንገድ ከማውጣት ይልቅ ዘመን አፈራሽ ቴክኖሎጂን መጠቀም መፍትሔ መሆኑም ተናግረው፤ በሕገ-ወጥና ባህላዊ በሆነ እንዲሁም በተከለከለ ስፍራ ማዕድን ከማውጣት ማህበረሰቡ እንዲቆጠብም የዞኑ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አሸናፊ ዳንቆ አሳስበዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ