ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከኢትዮጵያ ወደ ውጭ ሀገራት የሚላከው ደረጃ አንድ (እስፔሻል) የቡና ምርት ከዚህ ቀደም ከነበረው የ25 በመቶ ጭማሪ በማሳየት አጠቃላይ ድርሻው ወደ 45 በመቶ ማደጉን የቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል።
ከቡና ምርት ጥራት እና አያያዝ ተያይዞ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ችግሮች ይስተዋሉ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ "በተለይም በተለምዶ (ስፔሻል) የተሰኘውን ቡና በብዛት ከማምረት እና ውጭ ሀገራት ከመላክ አንጻር የነበሩትን ክፍተቶች እንዴት እየተፈቱ ነው? አሁን ያለበት ሁኔታስ እንዴት ይፈታል?" ሲል አሐዱ ጠይቋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የሰጡት የቡናና ሻይ ባለስልጣን የገበያ እና መረጃ ደህንነት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ቸሩ ኩሩ፤ የቡና ጥራት በተሻለ ሁኔታ ለማረጋገጥ እና ገቢን ለመጨመር እየተሰራ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በአጠቃለይ ሀያ በመቶ ብቻ እስፔሻል ቡና ወደ ወጭ ሀገራት ይላክ የነበረው፤ አሁን ላይ ከ40 እሰከ 45 በመቶ ደረጃ አንድ እና ሁለት እስፔሻል ቡና ወደ ዉጭ ሀገራት መላክ መጀመሩን አብራርተዋል።
አክለውም የጥራትን ጉዳይ በሚመለከት ከፍተኛ መሻሻሎች ስለመኖራቸው የገለጹ ሲሆን፤ አሁንም እንደ ሀገር ትኩረት ተሰቶ እየተሰራ ስለመሆኑ እና በቀጣይም ሙሉ ለሙሉ እስፔሻል የሆነ ቡናን ወደውጭ ለመላክ መታሰቡን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ የቡና ዘሮችን ከሚያመርቱ ቡና አምራች ሀገራት ተጠቃሽ ብቻ ሳትሆን ሰፊ የሆነ የቡና ተጠቃሚ የሚገኝባት ሀገር ብትሆንም፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሀገር ውስጥ የቡና ዋጋ በየጊዜው በእጥፍ እየጨመረ ስለመምጣቱ በመገለጽ ላይ ይገኛል።
ለዚህም 'በቅርብ ጊዜ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የውጭ ምንዛሬውን ከፍ በማድረጉ ነጋዴው ማህበረሰብ ቡናን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ከማዋል ይልቅ ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ ተጠቃሚ በመሆኑ ነው' ተብሎ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ነጋዴዎች የማክሮ ኢኮኖሚክ ማሻሻያውን ምክንያት በማድረግ ቀደም ሲል ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ሲውል የነበረ ቡና በዝቅተኛ ደረጃ ወደ ውጭ እየተላከ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ጭማሪ በሀገር ውስጥ ሽያጭ ላይ እንዲኖር እና ቡና ላይ እሴቶችን በመጨመር እስፔሻል ቡናን ኤክስፖርት ማድረግ ላይ ትኩረት በመሰጠቱ ምክንያት መሆኑ ተመላክቷል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ