ጥር 27/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአፋር ክልል በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ዜጎች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በተደጋጋሚ እየተከሰተ በሚገኘው የመሬት መንቀጥቀጥ ሳቢያ ብዙ ሰዎች ከመኖሪያቸው በመፈናቀላቸውን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች ጥቃት ጥበቃና መከላከል ከፍተኛ ባለሙያ ዘካሪያስ ደሳለኝ ገለጸዋል፤
በመሆኑም "ችግሩ የተፈጠረበት ቦታ ላይ ባለሙያ በመመደብ፣ ከክልሉ ጋር በመተባበር እንዲሁም በፌደራል ኮሚቴ ሥር በመሆን ችግር ያለባቸው ቦታዎች ላይ ሪፖርት እንዲደርሰን በማድረግ፤ መረጃን የማደራጀት ሥራ በሰፊው እየተሰራ ይገኛል" ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በተለይም የመሬት መንቀጥቀጡ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች የመደናገጥና የመፍራት ሁኔታ እንዳይኖር በብሔራዊ ስጋትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል የሚወጡ መረጃዎችን ታች ድረስ በማውረድና በቅንጅት እንዲሰሩ በማድረግ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መሠራታቸውን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል በክልሉ 2017 በጀት ዓመት 6 ወራት ውስጥ ዘርፈ ብዙ ማህበረሰብ ተኮር ድጋፍና ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን፤ የሴቶች ጥቃት ጥበቃና መከላከል ከፍተኛ ባለሙያው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም አዋሽና መተሀራ ላይ በመሬት መንቀጥቀጡ ሳቢያ ለተፈናቁሉ ዜጎች እራሳቸውን መጠበቅና መቋቋም የሚያስችል ስልጠና በጀት ተመድቦ እየተሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ይህን መሰልና ሌሎች ፆታን መሰረት ያደረገ ጥቃት ላይ እንዲሁም ሴቶችና ሕጻናትን ጨምሮ በአጠቃላይ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ በሌሎች ክልሎችም ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫና ሥራ መስራቱን ባለሙያው ጨምረው ተናግረዋል።
በአፋር ክልል በቅርቡ በተደጋጋሚ በተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ምክንያት፤ ከገቢረሱ ዞን ዱለሳ እና አዋሽ ፈንታሌ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ከ58 ሺሕ በላይ ዜጎች በጊዜያዊ መጠለያ ገብተው ድጋፍ እየተደረገላቸው ስለመሆኑ አሐዱ ከዚህ ቀደም መዘገቡ ይታወሳል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ