ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዩናይትድ ስቴትስ "ጋዛን ትወስዳለች" ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፤ ምናልባትም በአሜሪካ ወታደሮች አማካኝነት በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን የማስወጣት እቅድ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

ይህ የፕሬዝዳንቱ ሀሳብ ዓለም አቀፍ ትችቶችን እና ግራ መጋባትን አስነስቷል፡፡

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔትያናሁ እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በነጩ ቤተ-መንግሥት ተገናኝተው በእስራኤል-ጋዛ ጦርነት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡

Post image

ውይይታቸውን ተከትሎ ሁለቱ መሪዎች በጋራ በሰጡት የጋራ መግለጫ ላይ፤ ትራምፕ "አሜሪካ የጋዛ ሰርጥን ትጠቀልላለች፤ እኛም ለዚህም ሥራ እንሰራለን" ሲሉ በአካባቢው ላይ ያላቸውን ፍላጎት እንደ አዲስ አሳይተዋል፡፡

አክለውም "ጋዛን የእኛ ካደረግን በኋላ ያልፈነዱ አደገኛ ቦምቦችንና ሌሎች መሳሪያዎችን እናከሽፋለን፣ ፍርስራሾችን በማጽዳት በአካባቢው ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት የአሜሪካ ወታደሮችን የጋዛ ሰርጥ እናሰማራለን" ብለዋል፡፡

"ፍልስጤማውያን በጦርነት በተመሰቃቀለው ግዛት ውስጥ ከመቆየት ይልቅ ለመኖር የሚያመች፣ ጥሩ የሚያምር መሬት ሊሰጣቸው ይችላል" ሲሉም ጉዳዩን ከሰብአዊነት ጋር አያይዘው አቅርበውታል።

Post image

የሃማስ ባለስልጣናት ሃሳቡን "በክልሉ ውስጥ ሁከት እና ውጥረት ለመፍጠር ያለመ መመሪያ" በማለት የጠሩት ሲሆን፤ በጋዛ ያሉ ሰዎች "እነዚህ እቅዶች እንዲተላለፉ አይፈቅዱም" ማለታቸውን የሲኤንኤን ዘገባ አመላክቷል፡፡

ትራምፕ ከባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ጀምሮ ግብጽና ጆርዳን የተፈናቀሉ ጋዛውያንን ተቀብለው እንዲያስተናግዱ በተደጋጋሚ የጠየቁ ሲሆን፤ ሁለቱን ሀገራት ጨምሮ ሌሎች የአረብ ሀገራት የፕሬዝዳንቱን ሀሳብ በጽኑ አውግዘውታል።

ግብፅ፣ ዮርዳኖስ እና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ አጋሮች ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ማፈናቀል የመካከለኛው ምስራቅ መረጋጋትን አደጋ ላይ እንደሚጥል፣ ግጭቱን ሊያሰፋው እንደሚችል እና በአሜሪካና በሌሎች ተባባሪ ሀገራት በኩል በሁለቱ አካላት መካከል መፍትሄ ለማግኘት ለአስርት ዓመታት ያህል የተደረገውን ብርቱ ጥረት የሚያጠፋ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

Post image

በዚህም የአረብ ሀገራቱ ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ለማፈናቀል የሚቀርበውን ማንኛውም ሀሳብ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ የገለጹ ሲሆን፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ደግሞ "ይህ የዘር ማጽዳት ድርጊት ነው" ብለውታል።

ሳዑዲ አረቢያ ለፍልስጤም መንግሥት ያላትን "የማያወላውል" ድጋፍ በድጋሚ ማረጋገጧም ተነግሯል፡፡

የቀኝ ዘመሙ የእስራኤል ብሔራዊ ደኅንነት ሚንስትር በበኩላቸው፤ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረጉትንና ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ለማባረርና በግዛቱ ውስጥ የአይሁድ ሰፈሮችን ለማቋቋም ያነሱትን ሃሳቡ አወድሰውታል፡፡

ሚንስትሩ ኢታማር ቤን ጊቪር "የትራምፕ አስተያየቶች በጦርነቱ ወቅት እስራኤል የነበራትን አቋም የሚያግዝ ነው" ያሉ ሲሆን፤ ኔታንያሁ እንዲህ ዓይነቱን እቅድ እንዲቀበሉም አሳስበዋል።

የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሃማስ የጋዛን ግዛት ከ15 ዓመታት በላይ ያስተዳደረ ሲሆን፤ እ.ኤ.አ ጥቅምት 7 ቀን 2023 በእስራኤል ላይ ጥቃት በመሰንዘር 1 ሺሕ 200 ሰዎችን መግደሉንና 250 ሰዎችን አግቶ መወሰዱን ተከትሎ ሃማስ እና እስራኤል ወደለየለት ጦርነት ውስጥ ገብተዋል፡፡

በቅርቡም ሁለቱ ተፋላሚዎች በግብጽና ኳታር አደራዳሪነት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

Post image

በታሕሳስ ወር የወጣው የተባበሩት መንግሥታት የድርጅት የጉዳት ግምገማ ሪፖርት፤ ከእስራኤል የቦምብ ጥቃቶች በኋላ በጋዛ የተረፈውን ከ50 ሚሊዮን ቶን በላይ ፍርስራሽ ለማጽዳት 21 ዓመታትን ሊወስድና እስከ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር ሊፈጅ እንደሚችል አመላክቷል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ