የካቲት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአሁኑ ወቅት በገበያ ላይ የሚገኙ አብዛኞቹ ፈሳሽ እና ደረቅ ሳሙናዎች የኢኒስቲዩቱን ደረጃ ያላሟሉ መሆናቸው የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት አስታውቋል፡፡
በኢንስቲትዩቱ በደረጃ ዝግጅት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሥር የአከባቢ ጤና እና ደህንነት ዴስክ ኃላፊ የሆኑት አቶ ወርቁ አደፍርስ፤ የደረጃ መስፈርቶችን አሟልተው የሚያቀርቡ የዘርፉ አምራች ማህበራት ቢኖሩም አሁንም ከደረጃ በታች የሆነን ምርት ወደ ገበያ የሚያቀርቡ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
በተለያዩ ፈሳሽ እና ደረቅ የሳሙና ምርቶች ላይ የደረጃ ምዘናን የሚገልጽ ምልክት ተሰጥቷቸው በገበያ ላይ የሚገኙ ምርቶች መኖራቸውን የገለጹት ኃላፊው፤ ሆኖም በአሁኑ ወቅት ይህንን ምልክት የማይጠቀሙ ፈሳሽ እና ደረቅ ሳሙና አምራቾች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
አምራቾች ከኢንስቲትዩቱ የሚሰጠውን የደረጃ ማረጋገጫ ምልክት መጠቀማቸው በገበያው ያላቸውን ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምርም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
የዘርፉ አምራች ማህበራት የሚያመርቱት ምርት የማህበረሰቡን ደኅንነት አደጋ ላይ የማይጥል ለመሆኑ ኃላፊነት ሊወስዱ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም ሸማቹ የማህበረሰብ ክፍል ምርቶችን በሚገዛበት ወቅት የደረጃ መስፈርቱን ያሟሉ ስለመሆናቸው ትኩረት ሰጥቶ ሊመለለከት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በእሌኒ ግዛቸው
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
አብዛኞቹ በገበያ ላይ የሚገኙ ሳሙናዎች የደረጃ መስፈርቶችን ያላሟሉ መሆናቸው ተገለጸ
