የካቲት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ውስጥ ቁጥራቸው አነስተኛና ከ20 እስከ 30 የማይበልጡ የትራፊክ መብራት ምልክቶች የነበሩ ሲሆን፤ አሁን ላይ ግን ወደ 160 ማድረስ መቻሉን የአዲስአበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን አስታውቋል።
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የትራፊክ መብራቶችን ቁጥር ለማሳደግ በተሰራ ሥራ በተለይም የ2017 በጀት ዓመት 6 ወራት በርካታ ቦታዎች ላይ አዳዲስ የትራፊክ መብራቶች እንዲተከሉ መደረጉን የባለስልጣን መስሪያቤቱ ም/ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ኤልያስ ዘርጋው ለአሐዱ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የመቆጣጠሪያ ዘዴ የሌላቸው የመንገድ መጋጠሚያዎች ላይም መቆጣጠሪያዎች እንዲኖሩ የተሰሩ ሥራዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡
ከሌሎች የጥፋት አይነቶች ጋር ሲነፃፀር አልፎ አልፎ ተቆጣጣሪዎች በማይኖሩበት ጊዜና ምሽት ላይ ከሚፈጸም የደንብ ጥሰት በዘለለ አሽከርካሪዎች የትራፊክ መብራት ላይ የተሻለ አፈፃፀም እንዳለ የገለጹ ሲሆን፤ ጥፋቶችን ሙሉ ለሙሉ ለመከላከል በሰፊው እየተሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
አሁንም ግን በቂ የሚባል ባለመሆኑ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመግለጽ፤ አደጋዎችን ከመቀነስ አንፃር የአሽከርካሪዎች እና እግረኞች ባህሪም ከጊዜ ወደጊዜ መሻሻል እያሳየ ስለመምጣቱ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል መንገዶች ደህንነታቸው የተረጋገጠ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ብቻም 300 ኪሎሜትር የሚሆን የመንገድ ቀለም እና 30 ሺሕ ካሬ የሚሆን የእግረኞች ማቋረጫ ቀለም መቀባቱን ምክትል ዳይሬክተሩ ለአሐዱ ገልጸዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰላማዊ የሆነ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖርና ከመንገድ መሰረተ ልማት ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮች ለመቀነስ አምስት ዋና ዋና የሚባሉ የትኩረት መስኮችን በመለየት ማለትም በቁጥጥር፣ በትምህርትና ግንዛቤ፣ የፖርኪንግ አስተዳደርን ስርዓት በማስያዝ እንዲሁም በምህንድስና ማሻሻያ ሥራዎችና በቴክኖሎጂ በርካታ ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በመሆኑም በተለይም የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ መንግሥት ካለበት ኃላፊነት ባሻገር ማህበረሰቡ ተባባሪ በመሆን የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው አፅንኦት ሰጥተዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
በከተማዋ ውስጥ የነበሩ ከ30 የማይበልጡ የትራፊክ መብራቶችን ወደ 160 ማሳደግ መቻሉ ተገለጸ
