የካቲት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ ከተማ፣ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ የግል ይዞታቸው የነበረው ቦታ ሙሉ ማስረጃ እያላቸው በክፍለ ከተማው የአርሶ አደር ኮሚቴ በግድ ተወስዶብኛል ሲሉ ለአሐዱ ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡
ወ/ሮ እጅጌ በቀለ የተባሉት ቅሬታ አቅራቢ ቦታው የአርሶ አደር የይዞታ መሬት መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ ከአባታቸው የወረሱት መሆኑንና ይህንንም በፍርድ ቤት ያረጋገጡበትን ማስረጃ በማያዝ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 እንድፈጽምላቸው በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርቡም ምላሽ እንዳላገኙ አንስተዋል፡፡

አክለውም ከ3 ዓመት በላይ በለሚ ኩራ እንዲሁም ለ3 ዓመታት በየካ ክፍለ ከተማ በአጠቃላይ በመልካም አሰርተዳር ችግር ለ6 ዓመት ጉዳዩ እንዲጓተት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ችግራቸውን የሚረዳ እና አቤቱታችን የሚሰማ ባለመኖሩ ስለ ቦታው የማይመለከተው አካል እንዲይዘው ተደርጓል ብለዋል፡፡
የቦታው መገኛ በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ሲቪል ሰርቪስ ወንዝ ዳር አካባቢ እንደሆነ አንስተው፤ ከዚህ በፊት የካ ክፍለ ከተማ ቦታው በእርሳቸው ይዞታ እንደሚገኝ ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡
ሙሉ መረጃቸውንም አያይዘው ለወረዳ 13 እንዳቀረቡ የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዋ፤ "ጉዳዩ ከ3 ዓመት በፊት በየካ ክፍለ ከተማ ሥር እየታየ የነበረ ሲሆን በአዲሱ አሰራር ደግሞ ቦታው ወደ ለሚ ኩራ እንዲገባ ተደርጓል" ይላሉ፡፡

በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ቢያቀርቡም ‘ጠብቁ እልባት ይሰጣችኋል' እንዲሁም፤ ‘መሬቱ መሬት ባንክ ገብቷል' የሚል የማወዛገቢያ ሀሳቦችን ከመስጠት ባለፈ መልስ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡
በጊዜው ቦታውን ሊወስደው የቻለዉ የወረዳዉ የአርሶ አደር ኮሚቴ እራሱ የነበረ በመሆኑ፤ ቅሬታቸውን ሊቀበላቸው ፈቃደኛ አለመሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ይህንን ጉዳይ በተመለከተ አሐዱ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 የአርሶ አደር እና ከተማ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተቋም ወጋዬሁን አነጋግሯል፡፡
ኃላፊው በምላሻቸው ጉዳዩ እርሳቸው ወደ ኃላፊነት ከመምጣታቸው በፊት ጀምሮ የነበረ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ፤ የተነሱ ቅሬታዎችን በመረዳት በቦታው ተገኝተው ችግሩን ለመፍታት ወይንም ቦታውን ለመለካት የ‘ይገባኛል' ጥያቄ ስላለው መፍትሔ እስኪያገኝ ድረስ ቅሬታ አቅራቢዋ እንዲጠብቁ አሳስበዋል፡፡
ነገር ግን ጉዳዩን አስመልክቶ መጀመሪያ በአባ ገዳ እንዲስማሙ ደብዳቤ የተጻፉ ሲሆን፤ ካልሆነ በፍርድ ቤት እልባት እስኪሰጥ ድረስ እንዲጠብቁ የሚል ምላሽ የሰጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በሁለቱም ወገኖች የተካሰሱበትን ጉዳይ እልባት ካገኘ በሐላ እንጂ፤ የይገባኛል ጥያቄ እያለው መለካት እንደማይችሉ አክለው ገልጸዋል፡፡
አሐዱም ይህ ጉዳይ በሕጉ መሰረት እንዴት ሊታይ ይችላል ሲል የሕግ ባለሙያ እና ጠበቃ አቶ ባንተወሰን ግርማን አነጋግሯል፡፡
የሕግ ባለሙያው በምላሻቸው ማንም ሰው ሙሉ ማስረጃ ያለው ሰው በህጉ ሊዳኝ እንደሚችል አንስተው፤ ቦታው ወደ መሬት ባንክ ገብቷል ቢባልም ተገቢ ካልሆነ ማስረጃውን በመያዝ ጉዳዩን በፍርድ ቤት እልባት እንዲሰጠው ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ሙሉ ማስረጃ እያላቸው በመልካም አስተዳደር ችግር ምክያት ሰዎች ሊንከራተቱ እንደማይገባም ባለሙያው አንስተዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ