የካቲት 11/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ) የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት የአፍሪካ ማዕከል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከፍቶ ርክክብ ተደርጓል።

ማዕከሉ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተቀየሱ የልማት ግቦችን ለመተግበር እና በአፍሪካ አህጉር ዘላቂ ልማትን ለመስመዝገብ የሚረዱ ጥናት እና ምርምሮችን ለማከናወን የሚረዳ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ እንደ አህጉር 54 ሀገራትን በመወከል በኢትዮጵያ የሚገኝ ብቸኛ ተቋም መሆኑ ተነግሯል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ማዕከሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መከፈቱ በትምህርት ላይ የሚደረጉ ምርምሮች በቴክኖሊጂ የታገዙ እንዲሆኑ ለማድረግ ሰፊ ዕድል ይፈጥራል።

"የሚደረጉ የምርምር ሥራዎች በኢትዮጵያ የሚሰሩ ኢንዱስትሪዎችን ከፍ ለማድረግ ጠቃሚ ነው" ሲሉ ፕሬዝደንቱ ገልጸዋል።

የማዕከሉን እንቅስቃሴ ለማሳደግ ያለብንን ኃላፊነት ለመወጣት ዝግጁ ነን ያሉት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንቱ፤ ማዕከሉ ኢትዮጵያን እና አህጉሪቷን ተጠቃሚ ማድረግ አላማው መሆኑን አንስተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የዘላቂ ልማት ማስፈጸሚያ ከሆኑ ከሁለት ሺሕ የሚሆኑ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በትብብር ይሰራል ብለዋል።

Post image

ይህ ማዕከል የጥናትና ምርምር ሥራዎችን በማከናወን ለፖሊሲ አውጭዎች ግብዓት የሚሆኑ ሳይንሳዊ መፍትሔዎችን ያቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት(ተመድ) የዘላቂ ልማት መፍትሔ ጥምረት በአሜሪካ ኒውዮርክ፤ በአውሮፓ ፓሪስ እና በኤዥያ ኳራላምፑር ቀጣናዊ ማስተባበሪያዎች እንዳሉት ያሉት ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በትናንትናው ዕለት በይፋ የተከፈተው አራተኛው የአፍሪካ ማስተባበሪያ ቢሮ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የዘላቂ ልማት መፍትሔዎች ኔትዎርክ ፕሬዝዳንት ፕ/ር ጄፍሪ ሳክስ በ38ኛው የአፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) እና የመንግሥት ተጠሪ ከሆኑት ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ