ጥር 30/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብድር ወስደው በትግራይ ክልል የተሰማሩ የንግድ እና አምራች ድርጅቶች ከዚህ በፊት ከ2 ዓመት በላይ ተራዝሞ የነበረው የብድር መክፈያ ጊዜ፤ በድጋሚ እንዲራዘም የትግራይ ክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጠይቋል፡፡

ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ በክልሉ ለሚንቀሳቀሱ ለሁሉም ተበዳሪ ተቋማት የ18 ወራት የእፎይታ ጊዜ እንደተሰጠ የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት በሪሁን ሃፍቱ አስታውሰዋል፡፡

አቶ በሪሁን "የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከመጀመሪያው የ18 ወራት የእፎይታ ጊዜ በኋላ የአንድ ዓመት ተጨማሪ ጊዜ ቢሰጥም፤ በርካታ የንግድ ድርጅቶች የገንዘብ ግዴታቸውን መወጣት አልቻሉም" ብለዋል፡፡

" 'ይፈታል' ተብሎ የተጠበቀው ግጭትና አለመረጋጋት የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በማሳደሩ ኢኮኖሚውን ጎድቶታል፣ በርካታ የንግድ ድርጅቶችም ሥራቸውን በበቂ መጠን አልጀመሩም፣ በዚህም ምክንያት ብድራቸውን መመለስ ስለማይችሉ የመክፈያ ጊዜ ማራዘምን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ያስፈልጓቸዋል" ሲሉም ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡

የክልሉን እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትን ችግር ያስተዋለው የክልሉ ንግድ ምክር ቤት፤ ችግሩን ለማቃለል ከብሄራዊ ባንክ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ጋር እየተነጋገረ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡

በክልሉ ያለው የንግድ እንቅስቃሴ እና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እንዲያድግ የብድር መክፈያ ጊዜን ማራዘም ብቻ ሳይሆን የንግድ ተቋማቱ ተጨማሪ ብድርን ጨምሮ ሌሎች ማበረታቻዎች ሊደርግላቸው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ