ጥር 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የገለጹት በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች ጥቃት ጥበቃና መከላከል ከፍተኛ ባለሙያ ዘካሪያስ ደሳለኝ፤ በሀገሪቱ ጦርነትና የጎርፍ አደጋን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች በየጊዜው በሚፈጠረው በርካታ መፈናቀሎችና ማህበራዊ ቀውሶች የተፈጠረበት ሁኔታ ስለመኖሩ ለአሐዱ ተናግረዋል።

ቁጥራዊ መረጃውን የመቆጣጠር ጨምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰው ሰራሽም ሆነ በተፈጥሮ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማስተባበር በዋናነት ኃላፊነቱ የተሰጠው የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እንደሆነ አንስተዋል።

Post image

ሆኖም ግን ተፈናቃዮችን በተመለከተ ባለው ቅንጅታዊ አሰራር መሰረት ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርም የጥበቃና ከለላ ሥራን የማስተባበር ሥራ እንደሚሰራ በመግለጽ፤ "በተለያዩ መንገዶች የሚደርስባቸውን ችግሮች ለሚመለከተው አካል የማቅረብና አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው የማድረግ ሥራም ይሰራል" ሲሉ አክለዋል።

በመሆኑም ከኮሚሽኑ ጋር በቅንጅት በሚሰሩት ሥራ መሰረት አሁን ባለው ሁኔታ በሀገሪቷ ውስጥ በአጠቃላይ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚደርሱ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በዋናነትም በሴቶች፣ ሕጻናት አረጋውያን፣ የአካል ጉዳተኞችንና ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ድጋፍ በማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ እንደ አንሶላ፣ የሴቶች ንፅህና መጠበቂያና የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለተፈናቃዮች በጣም አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶች እንዲሟሉ የማስቻል ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በተጨማሪም የሥነ-ልቦናና የማህበራዊ ድጋፎችን በአማራ፣ ትግራይ አፋር፣ ኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉልና ሌሎች አካባቢዎች ላይ የአዕምሮ ጠባሳ እንዳይፈጠርና በማህበረሰቡ ውስጥ እርስ በርስ የመደጋገፍ ባህል እንዲዳብር የማድረግ ስልጠናዎች በሰፊው መሰጠታቸውን የሴቶች ጥቃት ጥበቃና መከላከል ከፍተኛ ባለሙያው ተናግረዋል።

አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ በጣም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ቢኖርም፤ ነገር ግን ሌሎች አጋር አካላትን በማስተባበር ከሞላ ጎደል ለሁሉም ተፈናቃዮች የተለያዩ ድጋፎች እየተደረጉ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ