የካቲት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ላለፉት አስር ዓመታት በጋዛ ታግቶ የነበረው አቶ አበራ መንግሥቱ የካቲት 15 ቀን 2017 ዓ.ም ተለቆ ወደ እስራኤል መግባቱን በቴል-አቪቭ የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስታውቋል።
ኤምባሲው አቶ አበራ ከእገታ ተለቆ ወደ ቤተሰቦቹ በመመለሱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።
ሐማስ ባለፈው ዓመት መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በፈጸመበት ጊዜ አግቶ ከወሰዳቸው አራት ሰዎችን ጨምሮ ስድስት የእስራኤላውያን ታጋቾችን ባሳለፍነው ቅዳሜ ለቅቋል።

ከተለቀቁት ታጋቾች መካከል በኖቫ የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ ታድመው ከነበሩት አራት እስራኤላውያን በተጨማሪ፤ የተፈቱት ሁለት ግለሰቦች ቤተ እስራኤላዊው አበራ መንግሥቱ እና ሂሻም አል ሰይድ ጋዛ ውስጥ ለዓመታት ቆይተዋል።
ትውልደ ኢትዮጵያዊው አበራ መንግሥቱ በአውሮፓውያኑ ከ2014 እና ሻሂም አል ሰይድ ደግሞ ከ2015 አንስቶ ነበር በሐማስ ቁጥጥር ሥር የቆዩት።
በወቅቱ ሐማስ ሁለቱ እስረኞች 'የእስራኤል መከላከያ ኃይል አባላት ናቸው' ቢልም፤ የእስራኤል ባለሥልጣናት ሰነዶችን ያየው ሂውማን ራይትስ ዋች ግን "ሁለቱም ከወታደራዊ አገልግሎት ውጪ የሆኑ ሲቪሎች ናቸው" ብሎ ነበር።
እስራኤል አበራ መንግሥቱን እና ሻሂም አል ሰይድን ለዓመታት ማስለቀቅ ሳትችል መቆየቷ፤ በቤተሰቦቻቸው እና በሲቪል ቡድኖች ዘንድ ተስፋ መቁረጥ ፈጥሮ መቆየቱም ተነግሯል።

3821 ቀን በእገታ ውስጥ ያሳለፈው አበራ ሐማስ በ2023 በሕይወት መኖሩን የሚያሳይ ቪዲዮ እስኪለቅ ድረስ ያለበትን ሁኔታ ማንም አያውቅም ነበር።
ከቤተ እስራኤላውያን ቤተሰቦቹ በአውሮፓውያኑ 1986 ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደው አበራ፤ ኢትዮጵያውያን አይሁዶች ወደ እስራኤል በተከታታይ በተወሰዱበት ወቅት ከወላጆቹ እህት እና ወንድሞቹን ጨምረው ወደ እስራኤል ሲያቀኑ የአምስት ዓመት ልጅ እንደነበር ተነግሯል።
እስራኤል ውስጥ አሽኬሎን በምትባለው ከተማ ውስጥ ከዘጠኝ እህት እና ወንድሞቹ ጋር ያደገም ሲሆን፤ በጣም ይቀራረቡ የነበረው ታላቅ ወንድሙ ሚካኤል መንግሥቱ መሞትን ተከትሎ በእጅጉ ማዘኑን እና እራሱን ማግለል መጀመሩን 'ኢዝራኤል ሃዮም' ድረ ገጽ ዘግቧል።
ከአስር ዓመት በፊትም በጀርባ የሚታዘል ቦርሳውን አንግቶ ከቤተሰቡ ቤት በመውጣት በጋዛ ሰርጥ እና በእስራኤል መካከል ወደተዘረጋው የደኅንነት ጥበቃ አጥር ማምራቱ ተገልጿል።
በስፍራው የነበሩ የእስራኤል ወታደሮች አበራ የደኅንነት ቀጣናውን እንዳያልፍ ለማስቆም ቢሞክሩም፤ እሱ ግን በአጥሩ ላይ በመንጠላጠል ወደ ጋዛ ሰርጥ ግዛት ዘሎ መግባቱም ተነግሯል።
ወታደሮቹ አበራ ከአፍሪካ የመጣ ስደተኛ እንጂ እስራኤላዊ መሆኑን ያወቁት የዜግነት መታወቂያውን ካገኙ በኋላ ነበር።
በሐማስ ቁጥጥር ሥር ወደ ምትገኘው ጋዛ ሰርጥ ሾልኮ የገባቸው አበራ መንግሥቱ ከዚያ በኋላ ደብዛው ጠፍቶ ከቆየ አስር ዓመት ሊሞላው በተቃረበበት ጊዜ በጥር 2023 (እአአ) ሐማስ በሰራጨው ቪዲዮ ላይ መታየቱ ተገልጿል።
በቪዲዮው ላይ ቤተ እስራኤላዊው "እኔ እስረኛው አበራ መንግሥቱ ነኝ። እስከ መቼ ነው እዚህ የምቆየው? ከዚህ ሁሉ የስቃይ ዓመታት በኋላ የእስራኤል መንግሥት የት ነው ያለው? ከዚህ ስቃይ ማነው የሚያድነን?" የእስራኤል መንግሥት ካለበት ሁኔታ እንዲያወጣው የሚማጸን መልዕክት አስተላልፎ ነበር።
አበራ መንግሥቱ ወደ ጋዛ በሄደበት ወቅት ዕድሜው 28 ዓመት የነበረ ሲሆን፤ ቤተሰቦቹ መለቀቁን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የ38 ዓመት ልጃቸው "10 ዓመት ከአምስት ወራት ከግምት በላይ የሆነ ስቃይ ውስጥ ነበር የቆየው" ማለታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።
አክለውም "በሕይወት እንዲመለስ በርካታ ጥረቶች ተደርገዋል። ጸሎታችን፣ ምልጃችን እና ጥያቄዎቻችን እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ መልስ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር" ብለዋል።

አበራ ከተለቀቀ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ከእርሱ እና ከቤተሰቡ ጋር መነጋገራቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።
"ደስ ብሎኝ ነው የማቅፍህ፤ አጠቃላዩ የእስራኤል ሕዝብም እንደኔው ዛሬ በአንተ ነጻ መውጣት በእጅጉ ተደስተዋል" በማለት የተሰማቸውን መግለጻቸውን የእስራኤል መንግሥት ድረገጽ ላይ የወጣው ዘገባ ያመለክታል።
አበራ መንግሥቱ ከእስር የተለቀቀበት ስምምነት በእስራኤል መንግሥት እና በሐማስ በኩል በተደረሰ ስምምነት መሠረት እስራኤል በመቆዎቹ የሚቆጠሩ እስረኛ ፍልስጤማውያንን እንዲለቅ፣ ሐማስ ደግሞ በእጁ ያሉትን ታጋቾች እንዲያስረክብ በተደረሰ ስምምነት ነው።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ