የካቲት 13/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ወደ ሀገር የሚገቡ የውጪ ባንኮችን በተመለከተ ዝርዝር ጉዳዩ በመመሪያ እንደሚወጣ በመጠቆም፤ የሚመጡበት ሀገር ግን ከኢትዮጵያ ጋር በዲፕሎማሲ ጥሩ የሆነ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚገባ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ መግለጻቸው ይታወሳል።

በመሆኑም ብሔራዊ ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ጥሩ ዲፕሎማሲ ግንኙነት ያላቸውን ሀገራት ለይቶ ባያስቀምጥም፤ በመመሪያው ላይ ለፋይናንሱ ዘርፍ ከሀገራት ወዳጅ መሆን ይልቅ ተወዳዳሪነታቸው ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አሐዱ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በገበያ ላይ በወዳጅ ሀገር ሥም ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ባንኮች የማይሻሉም ሊመጡ ስለሚችሉ ጥንቃቄ እንደሚያሻው የገለጹት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶ/ር ሞላ አለማየሁ፤ በመርህ ደረጃ የተሻለ የሚሆነው ወዳጅ ሀገር ብሎ ከመለየት ይልቅ ተወዳዳሪ የሆኑ ባንኮችን ማስገባት እንደሆነ ተናግረዋል።

ባንኮች ከወዳጅ ሀገራት እንዲመጡ የሚደረግበት ምናልባት በሀገራቱ በኩል ዋስትና የሚሰጣቸው ከሆነ ስጋትን ከመቀነስ አንፃር ሊጠቅም እንደሚችል የገለጹት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው፤ ተወዳዳሪነትን እንዳይገድብ ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጪ ከሚመጡ ባንኮች ጋር የእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ለማድረግ የሚያግዛቸውን አሰራር መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል።

ሌላኛው አሐዱ ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሙሀመድ አብራር በበኩላቸው የፋይናንስ ተቋማት ገለልተኛ በመሆናቸው የግዴታ በፖለቲካ ጉዳይ ግንኙነት አላቸው ማለት እንደማይቻል ገልጸዋል።

ከኢኮኖሚ አንፃር ሲታይ አገልግሎት መስጠት የሚችሉና ጠንካራ አቅም ያላቸው የፋይናንስ ተቋማት መሆናቸው እንጂ፤ ከወዳጅ ሀገር የመምጣታቸው ጉዳይ ፋይዳ እንደሌለውም ተናግረዋል።

በመሆኑም በፋይናንሱ ዘርፍ ወዳጅ ሀገራትን ማስቀደም በሌሎች ሀገራትም የተለመደ መሆኑን በማንሳት፤ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መስፈርት ግን ተጨማሪ ማብራሪያ የሚያስፈልገው እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በዚህ መስፈርት ከሆነ ወደገበያው የሚመጡት ከወዳጅ ሀገራት ብቻ ስለሆኑ ተፈቅዶላቸው ሌሎች የተደራጁና የሀገሪቱን ማነቆ የሆነ ችግር መፍታት የሚችሉ ጠንካራ አቅም ያላቸው ባንኮች እንዳይገቡ እንዳያደርግ ስጋት እንዳላቸው አክለው ገልጸዋል።

ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ባንኮችን በተመለከተ መንግሥት የራሱን መመዘኛ ማውጣት እንደሚችል የገለጹት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ፤ "ከኢትዮጵያ ጋር የትኞቹ ሀገራት የበለጠ ወዳጅነት አላቸውና የላቸውም የሚለው በግልፅ የማይታወቅ በመሆኑ በደፈናው ከወዳጅ ሀገራት የሚለው ኢኮኖሚያዊ ሀሳብ ሳይሆን ፖለቲካ አንደምታ ይኖረዋል" ብለዋል፡፡

ስለሆነም መንግሥት መመሪያው ላይ ይሄንን በደንብ ማጤን እንዳለበትና ብቃትና ተወዳዳሪነታቸው ላይ ትኩረት ሊያደርግ እንደሚገባው አፅንኦት ሰጥተዋል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ