የካቲት 12/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የአፍሪካ ሕብረት የመጨረሻ ቀን ላይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት እንዲሁም የህወሓት ሊቀመንበር በተገበኙበት የፕሪቶሪያው ውል አፈፃፀም ላይ ውይይት መደረጉ ይታወሳል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ ንግግር ያደረጉት በፕሪቶሪያው የውል ስምምነት ላይ እና ከዛም ውጪ ከፍተኛ የአደራዳሪነት ሚና የነበራቸው የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ፤ ከሰሜኑ ጦርነት በፊት በትግራይ ግዛት ሥር የነበሩና በፕሪቶሪያው ስምምነት ወቅት አወዛጋቢ የተባሉ አካባቢዎች መፍትሔ ላይ እስኪደረስ ድረስ "በገለልተኝነት" መቆየት አለባቸው በሚል መናገራቸው ቅሬታ አስነስቷል፡፡

በተለይም ቅሬታቸውን የገለጹት በቅርቡ ጥምረት የመሠረቱት በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱት ውድብ ናፅነት ትግራይ፣ ባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ እና አረና ሉዓሊዊ ትግራይ ፖርቲ ናቸው፡፡

Post image


ፓርቲዎቹ ባወጡት የጋራ መግለጫም የኦባሳንጆ ንግግር የትግራይ ግዛታዊ አንድነትን ያላከበረ እና የፕሪቶሪያውም ሰላም ስምምነት የጣሰ ነው ሲሉ ገልጸውታል፡፡

የውድብ ናፅነት ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ደጀን መዘገብ በበኩላቸው፤ "የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከሰሞኑ በተካሄደው የአፍሪካ ሕብረት ስምምነት ላይ እንደ ማዳመቂያ ሆኖ የቀረበ ነበር" ብለዋል፡፡

በሕብረቱ በተለይም ተሰናባቹን ሊቀመነበር የፕሪቶሪያው ውል ስምምነት እንደ ስኬት ታይቶላቸው መሸኛ ከማደረግ በዘለለ ዋነኛ የሕብረቱ ጉዳይ ማደረግ አልተፈለገም ሲሉም ገልጸዋል፡፡

"የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በዋናነት የትግራይ ግዛቶች ከጦርነት በፊት ወደ ነበሩበት ይመለስ የሚል እና ሕገ-መንግሥታዊ ስርዓቱ ከጦርነት በፊት ወደ ነበረው ይመለሱ የሚል ነው" የሚሉት ዶክተር ደጀነ፤ ይሁን እንጂ በኦሊሴጉን ኦባሳንጆ በኩል የተላለፈው መልዕክት ይህንን የስምምነቱን አንቀፅ የሳተ ነው ብለዋል፡፡

"የትግራይ መሬቶች በገለልተኝነት መቆየት አለባቸው ተብሎ በአደራዳሪው ግለሰብ የተላለፈው መልዕክት የትግራይን ግዛታዊ አንድነት ያላከበረ ነው" ሲሉ የሚገልጹት ደግሞ፤ የባይቶና አባይ ትግራይ ፓርቲ ሊቀመንበር ክብሮም በርሕ ናቸው፡፡

"ንግግሩ ሰምምነቱን የሚያፈርስ ነው" ያሉት አቶ ክብሮም፤ "ይህንን ስምምነት ከምንም በላይ ማሰከበር የነበረባቸው ሰው በመሆናቸው ለዚህ ንግግር ማስተካከያ ሊደረግበት ይገባል" ብለዋል፡፡

በሕብረቱ የመጨረሻ ቀን የፕሪቶሪያ ውል ስምምነት አፈፃፀም ላይ በነበረው ውይይት፤ አቶ ጌታቸው ረዳ እና ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ጨምሮ በርካቶች በመገኘት ውይይት አካሂደዋል፡፡

በዚህ መድረክ ላይ ንግግር ያደረጉት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፤ ሰላምን ከመስበክ፣ ሰላምን ከመተግበርም ሆነ ከምንም በላይ ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው የሚለሱበት ሁኔታ በፕሪቶሪያው ውልም ሆነ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ተፈፃሚ መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ