ጥር 29/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ቁጥጥር እና ፍተሻ ቢደረግላቸውም ሁሉም ምርቶች ላይ ባለመሆኑ የተለያዩ የጥራት ችግሮች እና ብልሽት ሲያጋጥማቸው ይስተዋላል።
እነዚህ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች በብዛት እና በዓይነት በርካታ በመሆናቸው እንዲሁም ሕገ-ወጥ ግብይቶች በመኖራቸው፤ ሁሉንም አይነት ምርቶች ለመፈተሽ አዳጋች ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን በተለይም የኤሌክትሪክ ገመዶች፣ ማከፋፈያዎች፣ ኬብሎች እና የአምፖል ምርቶች ላይ አስገዳጅ የቁጥጥር ሥራዎች እንደሚሰራ በሚኒስቴሩ የአዲስ አበባ ኮሚቴ ጽ/ቤት ኃላፊ ገብረጊዮርጊስ አበራ ለአሐዱ ገልጸዋል።
ኃላፊው አክለውም "ነገር ግን አንዳንድ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች ቁጥጥር ላይ በአስገዳጅነት የጥራት ፍተሻ ስለማይደረግላቸውና ጉዳት የሚያስከትሉ በመሆኑ፤ በቀጣይ ሌሎች ምርቶች ላይ የአስገዳጅነት ደረጃና ቁጥጥር ለመጨመር እየተሰራ ነው" ብለዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ማብራሪያ የሰጡት በኢትዮጵያ ተስማሚነት እና ምዘና ድርጅት የኤሌክትሪክ ፍተሻ ላብራቶሪ ቡድን መሪ ታጠቅ ሽፈራው፤ ከውጭ ሀገራት የሚገቡ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እና የሌሎች ምርቶች ጥራትን ለመመርመር የሚያስችል የግብዓት እጥረት መኖሩኔ ገልጸዋል።
ለዚህም በሀገር ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እንዲሁም ሌሎች የሕክምና ቁሳቁሶችን የጥራት ደረጃ ለመመርመር የሚያስችል መመርመሪያ መሳሪያዎች እጥረት መኖሩ በምክንያትነት አንስተዋል።
ይህን ችግር ለመፍታትም ከውጭ ሀገር የሚገቡትን እንዲሁም በሀገር ውስጥ የሚመረቱትን ምርቶች ለመመርመር የሚያስችል በቂ ቁሳቁስ ባይኖርም፤ ልዩ ትኩረት የሚያስፈልግቻውን ምርቶች በመለየት በሌሎች የውጭ ሀገራት የጥራት ደረጃ እንዲያልፉ እየተደረገ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
አክለውም እንደ ሀገር ይህን ችግር እና የመመርመርያ ግብዓት እጥረት ለመቅረፍ ከንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እንዲሁም ከዓለም አቀፍ ሀገራት ጋር እየተሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ከውጭ ሀገራት የሚገቡ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶችን ጥራት የሚያረጋግጥ የጥራት ፍተሻ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
የምርቶቹን ጥራትን ለመመርመር የሚያስችል የግብዓት እጥረት መኖሩ ተነግሯል
