ጥር 28/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በንግድ ቢሮ ከተተመነው ግራም በታች ሲሸጡ የተገኙ ከ70 በላይ ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ያስታወቀ ሲሆን፤ በቀጣይም በሁሉም ዳቦ ቤቶች ላይ የሚያደርገውን ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከ70 ከግራም በታች የሆነ የዳቦ ምርት ለሸማች እንዳያቀርቡ የቁጥጥር ሥራ እያከናወነ እንደሚገኝ፤ የቢሮ የንግድ ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር ቅድስት ስጦታው ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
![Post image](/_image?href=https%3A%2F%2Fcdn.sanity.io%2Fimages%2Fbede4k7t%2Fproduction%2F6dee9e4a263da35c1b7b2c50cd6b293a307fe3e3-526x526.jpg&w=526&h=526&f=webp)
ምክትል ዳይሬክተሯ አክለውም ቢሮው በዳቦ ምርት ላይ የዋጋ ተመን እንደማያወጣ የገለጹ ሲሆን፤ "ሆኖም በከተማዋ በሚገኙ ዳቦ ቤቶች ላይ በቢሮው ከተተመነው ግራም በታች የሆነ ምርት ለገበያ እንዳይቀርብ እየተሰራ ይገኛል" ብለዋል፡፡
በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ በሚገኙ ዳቦ ቤቶች ላይ ከተቀመጠው ግራም መጠን በታች የሆነ ምርት እንዳይቀርብ ከዳቦ ቤቶች ናሙና በመውሰድ የተተመነውን መጠን የልኬት ሥራ የሚቆጣጠሩበት አሰራር ስለመኖሩ ምክትል ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡
በንግድ ቢሮው በስድስት ወራት ውስጥ በተከናወነ የቁጥጥር ሥራም፤ ከ70 በላይ ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግረዋል፡፡
ቢሮ በክትትል ወቅት በሚያገኛቸው ከግራም በታች የሆነ መጠን ያለው ምርት በሚሸጡ ዳቦ ቤቶች ላይ ከጽሁፍ እስከ ንግድ ፈቃድ የመሰረዝ እርምጃ የሚወስድበት አሰራር ስለመኖሩ ኃላፊዋ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ