የካቲት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በደቡብ ወሎ ዞን ቃሉ ወረዳ የሰባት ዓመት ሕጻን ልጅ አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በ17 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣና ከማንኛውም ሕዝባዊ መብቶች እንዲታደግ መወሰኑን የቃሉ ወረዳ ፖሊስ አስታውቋል።

ተከሳሹ በእስራት ሊቀጣ የቻለው ታሕሳስ 14 ቀን 2017 ዓ.ም ቃሉ ወረዳ 029 ቀበሌ ልዩ ቦታው ገረገራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ተከሳሽ ከድር ይመር መሀመድ የ 7 ዓመት ሕጻን ልጅ አስገድዶ በመድፈሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የወረዳው ፖሊስ ከማህበረሰቡ ስለወንጀሉ በደረሰው ጥቆማ መሰረት ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ሥር ካደረገ በኋላ የምርመራ መዝገቡን በሰውና በቴክኒክና በታክቲክ ማስረጃ ካጠናቀረ በኋላ መዝገቡን ለሚመከተው የፍትህ አካል ልኳል።

የደቡብ ወሎ ዞን ከፍተኛ ፍረድ ቤትም ጉዳዩን ሲመረምር ከቆየ በኋላ ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ፤ የካቲት 04 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት በ17 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እና ለ 4 ዓመት ያህል ከማንኛውም ሕዝባዊ መብቶች እንዲታገድ ተወስኖበታል ሲል የቃሉ ወረዳ ፖሊስ ኮሙኒኬሽንና ሚዲያ ክፍልን ጠቅሶ የደቡብ ወሎ ዞን ፖሊስ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዘግቧል።

#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ