የካቲት 7/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) በአዲስ አበባ የሚገኙ የተለያዩ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ላለመጠናቀቃቸው ዋነኛ ምክንያት፤ ከወሰን ማስከር ጋር ተያይዞና መሰረተልማቶች በፍጥነት አለመነሳታቸው እንደሆነ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን አስታውቋል።
በዚህ ወቅት በርካታ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መኖራቸውን የገለጹት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እያሱ ሰለሞን፤ "ከእነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ወደ ማጠናቀቂያ ምዕራፍ እየተሸጋገሩ ያሉና በቅርቡ የሚመረቁ ናቸው" ብለዋል።
ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ሥራቸው የዘገዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች ስለመኖራቸውም ኃላፊው ለአሐዱ ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል ከአውቶቡስ ተራ በመሳለሚያ ወደ 18 ማዞሪያ የሚወስደው የመንገድ ግንባታን በመጥቀስ፤ ይህም ከአሌክሳንደር ፑሽኪን አደባባይ ወደ ጎተራ ከሚወስደው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ጋር በተመሳሳይ ጊዜ መጀመሩን ገልጸዋል።
ነገር ግን ግንባታውን በፍጥነት ለማጠናቀቅ ወሰን በማስከበር ሂደት ውስጥ በርካታ መነሳት ያለባቸው ቤቶችና የተለያዩ መሰረተ ልማቶች በመኖራቸው የገለጹ ሲሆን፤ በወቅቱ ባለመነሳታቸው ምክንያት የግንባታ ሥራው በሚፈለገው ፍጥነት መከናወን ሳይችል መቆየቱን ገልጸዋል።
በሌላ በኩልም "ከአየር ጤና ወለቴ የሚወስደው መንገድ በተመሳሳይ ሁኔታ የግንባታ ውል ከተደረገ የቆየ ቢሆንም፤ ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ በነበሩ ችግሮች ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ የግንባታ ሥራው መከናወን ባለመቻሉ መጓተቶች ታይቶበታል" ብለዋል።
በዚህም መሰረት አጠቃላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ 5 ነጥብ 7 ኪሎሜትር አካባቢ ርዝመት ያለው ሲሆን፤ 2 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር የሚሆን የወሰን ማስከበር ሥራ በተጠናቀቀባቸው መስመሮች ብቻ ግንባታው እየተከናወነ እንደሚገኝ አንስተዋል።
በመሆኑም አሁን ላይ የግንባታ ሥራዎች በፍጥነት እንዲከናወኑ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ለመስራት ጥረት እየተደረገ ስለመሆኑም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አስታውቀዋል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
ወሰን የማስከበር ሂደትና የመሰረተ ልማቶች በፍጥነት አለመነሳት ለመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መጓተት ምክንያት መሆኑ ተገለጸ
