የካቲት 18/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ እየተካሄደ ባለው የጥገና ሥራ ምክንያት የኃይል ማመንጨት ሥራው መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን፤ እየተካሄደ ባለው የጥገና ሥራ ምክንያት የኃይል ማመንጨት ሥራው መቋረጡን ገልጸው፤ በአሁኑ ሰዓት የደረቅ ቆሻሻ የማቃጠል ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ምስረታውን ያደረገው፤ በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኝ የደረቅ ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ያለመ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በ2011 ዓ.ም በሙከራ ደረጃ ኃይል ማመንጨት የጀመረውና በ2 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የተገነባው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ፤ ከጥር ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ የኃይል ማመንጫ ተርባይኑ ላይ ባጋጠመው ብልሽት ምክንያት ከአንድ ዓመት በላይ ኃይል የማመንጨት ሥራውን ተቋርጦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይህንንም ተከትሎ ጣቢያው ጥገና ተደርጎለት ከግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ ኃይል የማመንጨት ተግባሩን በግማሽ ቀንሶ እየሰራ የቆየ ሲሆን፤ ከመስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ግን ተርባይኑ ተጠግኖ በሙሉ አቅሙ ኃይል ሲያመነጭ ቆይቷል።
የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨት ባሻገር በመዲናዋ በቀን በአማካይ ከሚሰበሰበው 2 ሺሕ 500 ቶን በላይ ደረቅ ቆሻሻ 1 ሺሕ 280 ቶኑን እንዲቃጠል ያደርጋል ተብሏል።
ጣቢያው ከዚህ ቀደም በዓመት በአማካይ 185 ጊጋ ዋት ሰዓት ያመነጭ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሞገስ፤ ጥገናው ሲጠናቀቅ ሃይል የማመንጨት ሥራውን እንደሚቀጥልም ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ከመዲናዋ ተሰብስቦ የቀረበለትን 456 ሺሕ 898 ቶን ቆሻሻ ማስወገዱን ያስታወቀ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ 109 ሺሕ 608 ቶን ለኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫነት መዋሉን መግለጹ ይታወሳል፡፡
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
የረጲ የደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ኃይል ማመንጨት ማቆሙ ተገለጸ
